በኢአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የስራ አስፈጻሚ አባል ያልሆኑ መገኘት አነጋጋሪ ነው ተባለ

ባሁን ሰሃት የወያኔ ኢአደግ ስርሀትን ለማስቀጠል ስራ አስፈጻሚዉ ስብሰባ ላይ መጠመዳቸው ይታወቃል።
ይህ ስራ አስፈጻሚ  ነባር የሆኑትን ባሁን ሰሃት ግን ከስራ አስፈጻሚነት የተነሱት የህወሀት ባለስልጣኖችና ሌሎችም መገኘት የህወሀትን ጭንቀትና የቀድሞው ተሰሚነቱን ማጣቱ አስቆጭቶት ያንን ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት አንዱ አካል መሆኑ ተነግራል።
ህወሀት ከገባበት አጣብቂኝ ያወጡኛል ያላቸውን በስብሰባው ላይ መገኘት የማይገባቸው እንደ በረከትና አባይ ፀዐዬ የመሳሰሉትን አስቀምጦ ውጥረት በተሞላው መልኩ ጭቅጭቁ ተጣጡፋል የተለመደው ማስፈራርያ በኦህዴድ ባለስልጣናት ላይ ይሰነዘራል ።

ህወሓቶች የመጣው ይምጣ እያሉ ያስፈራራሉ። ኦህዴድን በተደጋጋሚ ይከሳሉ። ብአዴንንም አልፎ አልፎ ያነሳሉ። በህወሃቶች ዘንድ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ምስቅልቅል ሁኔታ ኦህዴድን ተጠያቂ እያደረጉ ተናግረዋል። አባይ ጸሃዬ እና ደብረጺዮን በዋናነት ኦህዴድ ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል።

አቶ በረከት ስምዖን አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አያስፈልግም መጀመሪያ መከላከያ አገሪቱን ያረጋጋና ከዛ ብኋላ ይመረጣል እያለ ነው። በእሱ ስሌት መሰረት ወታደሩ እዛም እዛም የሚታዩትን ተቃውሞዎች ደብዛቸውን ካጠፋ ብኋላ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ማንም ስለሌለ የዛንጊዜ የፈለግነው ጠቅላይ ሚኒስተር መሰየም እንችላለን ከሚል ነው፡፡

በረከት ዶ/ር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስተር መሆን የለበትም የሚል አቋም ይዞ በስብሰባው እና ከስብሰባው በኋላ ባለው የእረፍት ጊዜ ሌሎችን ሎቢ ሲያደርግ ተስተውሏል። የተወሰኑ የህወሃት አባላት ደብረጺዮን ጠቅላይ ሚኒስተር ይሁን እያሉ ነው። ይህ የማይሆን ከሆነ ምክትሉ ከኛ ይሁን በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል። ጌታቸው አሰፋ አሁን ደብረጺዮንን ጠቅላይ ሚኒስተር ማድረግ አሁን ካለው የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር ፈጽሞ መሆን የሌለበት ነው በማለት አቋሙን ገልጿል። በህወሃት መካከል ቀጣይ ማን ጠቅላይ ሚኒስተር ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ ሙሉ በሙሉ አንድ አይነት አቋም እንደሌለ ታይቷል::

እስካሁን ያለውን የሃገሪቱ ሁኔታም እየገመገሙ ነው፡፡ በረከተ በስብሰባው ላይ ዋና ተዋናይ ሆኗል።ስብሰባው እንደቀጠለ ነው።

 

በእስር ላይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድረሱልን እያሉ ነው

ቦረና አበራ፣ ወየቻ ታምሩ፣ ወሰኑ ገረመው፣ ዮሃንስ ፉርጋሳ፣ ገዳ ገመቹ፣ እዮብ ሙሊሳ እና ሳሎ ነጋሳ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢንጅነሪንግ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ለእስር ተዳርገዋል።

የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ምክንያት በነበረው ሕዝባዊ ንቅናቄ ማዕከላዊ አራት ወራት ከታሰሩ በኋላ “ወንጀሉ በተፈፀመበት አካባቢ ይዳኙ” ተብሎ ሚያዝያ 28/2008 ወደ ዲላ ከተማ ተዛውረዋል። ሀምሌ 7/2008 ዓም ወደ ሀዋሳ ተዛውረው በእስር ላይ ይገኛሉ።

የካቲት 7/2010 በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ቦረና አበራ በነፃ ሲሰናበት፣ ቀሪዎቹ እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል። ተከላከሉ ከተባሉት 6 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ሳሎ ነጋሳ (4ኛ አመት ተማሪ የነበረ) ብቻ “እከላከላለሁ” ሲል ወየቻ ታምሩ (የ3ኛ አመት ተማሪ)፣ ወሰኑ ገረመው (3ኛ አመት)፣ ዮሃንስ ፉርጋሳ (3ኛ አመት)፣ ገዳ ገመቹ (3ኛ አመት) “አንከላከልም” ብለዋል።

ተከሳሾቹ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የታሰሩ በመሆናቸው ችግር ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል። “የሚረዳን የለም፣ ሚዲያም እያስታወሰን አይደለም” ሲሉም ገልፀዋል።በጌታቸው ሺፈራው

 

የአርበኞች ግንቦት 7 አባላቶች በተጠኑ ሥፍራዎች ላይ 800 በራሪ የአርበኞች ግንቦት ሠባት የትግል ጥሪ ወረቀቶች ተበተኑ!

በደቡብ ወሎ ዞን ሀይቅ ከተማ አሥተዳደር ዛሬ ህዳር 29 ቀን እለተ አርብ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላቶች በተጠኑ ሥፍራዎች ላይ 800 በራሪ የአርበኞች ግንቦት ሠባት የትግል ጥሪ ወረቀቶች ተበተኑ::

በከተማው ማለትም አሥመራ በር ቀቀዋ በዴሴ ከተማ መግቢያ እና መውጫ በሆነችው ቢሻናቆ በሃይቅ በገባያ ማእከል በመሣናዶ እና በኮሌጅ ትምህርት ቤት መግቢያ እና መውጫ እንድሁም በመከነ እየሡሥ ባለው መግቢያ እና መውጫ በሮች የተበተኑት በራሪ ወረቀቶች በከለርድ የተዘጋጁ እና የተቆራረጡ በመሆናቸው ህብረተሠቡ በቀላሉ በኪሡ ይዞ እንድያሠራጮቸው ታሥበው የተዘጋጁ ከመሆኑ በተጨማሪ በሃይቅ ከተማ ትልቅ ገባያ በሚውልበት አርብ ገበያ ላይም ተበትኖል::

በዚህም ገባያ ከሀይቅ ከተማ አዋሣኝ ወረዳዎች የገጠሩም ሆነ የከተማው ህብረተሠብ ነጋዴው ተማሪን ይሁን አርሶ አደሩ ቀሥቃሽ በራሪ ፅሁፎቹን በእጃቸው እንዲገባ ለማድረግ ታቅዶ የተበተነ ሲሆን በተለያዩ ግርግዳ እና የመብራት ፖሎቹም ላይ ተለጥፈዋል በሶስት አቅጣጫ ለወረቀት ብተና በህብኡ የተደራጁ አባላት በተባለው ሥፍራ እና ጊዜ የበራሪ ፅሁፎቹን ለመበተን የወጡ አባሎቻችን በሠላም ወደ አሉበት ሥፍራ ተመልሠዋል፡፡

በቀጣይም በተጠናና በተደራጀ ሁኔታ በህወህት ሆድ አደር አፋኝ እና አሥገዳይ ግለሠቦች ላይ እርምጃ እንደምንወሥድ እንገልፃለን። አርበኞች ግንቦት 7 የሰሜን ኢትዮጵያ እዝ፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ስልጣን የለውም ተባለ

በጌታቸው ሺፈራው
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን አጥቷል ሲል ብይን ሰጥቷል። ጥቅምት 23/2010 በእነ ብርሃኑ ሙሉ እና ነጋ የኔው ክስ መዝገብ ስር ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ወንጀሉን ፈፀሙት የተባለው በአማራ ክልል በመሆኑ በወንጀለኛ ወቅጫ ህግ ስ/ስ/ቁ 99 እና 100 መሰረት ወንጀሉ ተፈፀመበት በተባለው ቦታ ክሱ ሊታይ እንደሚገባ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣንን ስላጣ ጉዳዩን ሊያይ አይችልም ሲል በአብላጫ ድምፅ በይኗል።
ፍርድ ቤቱ የክልል ፍርድ ቤቶች የፌደራል ፍርድ ቤት ስልጣን የተሰጣቸው ኢትዮጵያ በአህዳዊ መንግስት ትተዳደር በነበረችበት ወቅት እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምትተዳደረው በፌደራል ስርዓት ስለሆነ የስነ ስርዓት ህጉ ተፈፃሚ አይሆንም ሲል በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ በአብላጫ ድምፁ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 78 ለክልል ፍርድ ቤቶች የፌደራል ስልጣን የሰጣቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2/3ኛ ድምፅ በክልሎች የፌደራል ፍርድ ቤት እስኪቋቋም ብቻ መሆኑን ገልፆአል።
በአዋጅ ቁጥር 322/95 መሰረት በጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣አፋር፣ ሶማሊና ደቡብ ህዝቦች ክልየፌደራል ፍርድ ቤቶች ስለተቋቋሙ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ ወቅት የፌደራል ፍርድ ቤት ስልጣኑን አጥቷል የሚል ብይን ተሰጥቷል። የችሎቱ የማህል ዳኛ በአምስት ክልሎች የፌደራል ፍርድ ቤት መቋቋሙ የሌሎች ክልሎችን የፌደራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን አያስቀርም በማለት የልዩነት ድምፅቸውን አስመዝግበዋል።
የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ከሰጠው ብይን በተቃራኒ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጡ ጉዳዮች እየዳኘ የሚገኝ ሲሆን በአብነትም የኮለኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ የ”ሽብር” ክስ የቀረበባቸውን ሌሎች ተከሳሾች ጉዳይ እያየ ይገኛል። በኦነግና ግንቦት ሰባት ክስ ቀርቦባቸው ወንጀሉ ተፈፀመበት በተባለባቸው ክልሎች እንዲታይ ያቀረቡት ተቃውሞ ውድቅ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው የፍርድ ቤቶቹ ብይን ከህገ መንግስቱ የሚቃረን መሆኑን በመግለፅ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ አለልኝ ምህረቱ ” ዛሬ የሰማሁት ብይን በባህሪው እንግዳ ነው። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ስልጣን አጥቷል መባሉ የህግ ባለሙያዎችን ሊያነጋግር የሚችል ጉዳይ ነው” ብለዋል። ጠበቃ አለልኝ በብይኑ ስለማይስማሙም ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማቅረብ እንዳሰቡ ገልፀውልኛል።
እነ ብርሃኑ ሙሉ እና እነ ነጋ የኔው በቀረባቸው ክስ ላይ ያቀረቡት ሁሉም መቃወሚያ ውድቅ ተደርጎ አቃቤ ህግ የጠቀሰባቸውን የሰው ምስክር ለመስማት ለህዳር 20/2010 ቀጠሮ ተይዟል። አቶ ነጋ የኔው የወልቃይት ህዝብ አማራ ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባል እንደነበሩ የ ተገለፀ ሲሆን ጎንደር ከተማ ውስጥ ጥቃት ፈፅማችኋል ተብለው ተከሰዋል።

የአቶ በረከት መልቀቂያ ዜናና የሕወሐት ሴረኝነት

 

ይልቃል ጌትነት

አሁን ባለንበት ሁኔታ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ከባድ ችግር ውስጥ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ያለበትን የውስጣዊ ችግር የእድገት ደረጃ በጥሞና ለመረዳት እያንዳንዱን ክንዋኔ በጥንቃቄ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ የውስጣዊ ድርጅት ሽኩቻውን በአጠቃላይ ሀገራዊ ፖለቲካ ፋይዳው ጋር ሚዛን በመስራት ለእውነት የተጠጋ ትንተና ላይ ለመድረስ ሁለቱን ማለትም የድርጅት ውስጣዊ ሽኩቻውንና ሀገራዊ ፋይዳውን ሚዛን ላይ አስቀምጦ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሕወሐት እጅግ ሚስጥራዊ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሀገሪቱን የመምራት ኃላፊነትም በእነሱ ትክሻ ላይ መውደቁን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሀገራዊ ምስቅልቅል ውስጥ የአቶ በረከትን መልቀቂያ ይፋ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ለዚህ ጥያቄ ለእውነት የቀረበ መልስ ለማግኘት ሁለት መላምቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡


አቶ በረከት የድርጅቱ ጭንቅላት እንደሆኑ ይታመናል፡፡ አቶ አባዱላ የይስሙላ ፓርላማም ቢሆን በዓለም አቀፍ ግኝኙነት ደረጃ ሲታይ የነበሩበት ቦታ ትልቅ ገፅታ ነው፡፡ የእነዚህ ባለስልጣኖቸ መልቀቅ ሕወሐት/ኢሕአዴግ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞና ሁሉንም ነገር መቆጣጠር አቅቶት ባለስልጣኖቹ ተስፋ በመቁረጥና በመደናገጥ ሀገራዊ ኃላፊነት መውሰድ የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው በግላቸው እየወሰኑ ነው ማለት ነው፡፡በመሆኑም እነዚህ ትልልቅ ባለስልጣኖች በእንድ ጊዜ ስልጣን መልቀቃቸው ከፍተኛ ችግር መኖሩንና ለሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ መቃረባችንን መገመት ይቻላል፡፡


ሌላው በአሁኑ ሰዓት ኦህዴድ ከሕወሐት የበላይነት በብዙ መልኩ የማፈንገጥ አዝማሚያና በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር አጀንዳ መጋራትና የአላማ መደበላለቅ አለ ብሎ ሕወሐት ያምናል፡፡ የአባዱላ ገመዳ መልቀቅና ለመልቀቁ የሰጠው ምክንያት የኦሮሞን ህዝብ ለማነሳሳትና አባዱላ የህዝባዊ እንቅስቃሴው ቀጥተኛ ያልሆነ መሪ /informal leader/ ለመሆን በኦሮሞ ፖለቲከኞች የተቀነባበረ ነው በሚል ሕወሐት ይህንን የድርጅት ሽኩቻ ሚዛን ለማስጠበቅ የአቶ አባዱላን መልቀቅ በህዝብ ዘንድ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያው ያገኘውን የዜና ሽፋን ለመበረዝና በአባዱላ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን የፖለቲካ ትኩሳት ዝቅ አድርጎ ማሳየት ስለነበረበት አቶ በረከት በተመሳሳይ ሁኔታ ከስራ እንዲለቁና የዜና ሽፋኑን እንዲቆጣጠረው አድርገዋል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡

ይህንን ግምት የሚያጠናክረው ሕወሐት እጅግ ሚስጥራዊ ድርጅት መሆኑ፣አቶ በረከት ይሰሩበት የነበረው ቦታ ከህዝብ ገፅታ የራቀ በመሆኑ ዜናውን በአሁኑ ደረጃ ይፋ ሳያደርጉ በዝግታ መልቀቅ የሚችሉበት እድል ሰፊ በመሆኑ፣አቶ በረከትም በድርጅቱ ውስጥ ያላቸው ቦታ ከፍተኛና ሴራን ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው፣በድርጅትም ሆነ በሀገራዊ ፖለቲካ የእሳቸው መልቀቅ ዜና ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው ድርጊቱ ታስቦና ታቅዶ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በፖለቲካ ስራ ውስጥ አንድ ከባድ አደጋ ሲያጋጥም ያንን ዜና ለመሸፈንና አቅጣጫ ለማስቀየር አዳዳዲስ ዜናዎች ፈጥሮ አቅጣጫ ማስቀየርና ችግሩን ለመፍታት ትንፋሽ የማግኛ ዘዴ አድርጎ መጠቀም የተለመደ ተግባር ነው፡፡


ለማጠቃለል አሁን ያለው እውነታ በተራ ቁጥር 1 ተገለፀው ከሆነ ሀገራችን በፈጣን የለውጥ ማዕበል ላይ ስለሆነች ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን በጥንቃቄና በአስቸኳይ ከባድ ሀገራዊ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ያለው እውነታ በተራ ቁጥር 2 ላይ የተገለፀው ከሆነ የውስጥ የድርጅት ሽኩቻ ለትግሉ ከፍተኛ አስተዋፆ ቢኖረውም ጊዜ የሚሰጥና በተረጋጋ ሁኔታ አስቦ ትግሉን ለመምራት የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡