ወያኔ አርበኞች ግንቦት 7 የከፈተበትን ጦርነት ከህዝብ ለመደበቅ እየሞከረ ነው

የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች በተለያዩ ቦታዎች የወያኔን ሃይል ገጥመው የወያኔ መኮንኖችን ጨምሮ በርካታ የወያኔ ሰራዊት አባላትን እንደገደሉ በቃል-አቀባያቸው አማካኝነት ለኢሳት ቴሌቪዥን ገልጸዋል።

በወያኔ ዘረኛና ግፈኛ አገዛዝ የተንገፈገፈው የኢትዮጵያ ህዝብም ጆሮውን አቅንቶ ሁኔታውን በመከታተል ላይ ነው። ቀድሞውንም የወያኔ ሥርዓት ያለ ሃይል ትግል አይንበረከክም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካም ሆነ የሥርዓት ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉት ተባብረው በወያኔ ላይ ክንዳቸውን ሲያሳርፉ ብቻ ነው ብለው የሚያምኑት ኢትዮጵያውያን አርበኞች ግንቦት 7 በወያኔ ላይ የከፈተውን ማጥቃት በከፍተኛ ደስታ ነው የተቀበሉት።
አንዳንዶች አርበኛውን በገንዘብ ለመደገፍ እና ለማጠናከር ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ በወያኔ ጎራ በኩል ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምንም የተሰማ ነገር የለም። ጥያቄው… ለወትሮው ትንሽ ትልቁን “የግንቦት 7” አባል ነው ብሎ በመፈረጅ ንጹሃንን እስርቤት የሚወረውረው ወያኔ በይፋ ስለተከፈተበት ጦርነት ለምን ዝምታን መረጠ? ነው።
ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ ሥርዓት ህዝብ እጅግ እንደጠላውና ሆ ብሎ ሊነሳበት እንዳቆበቆበ ይረዳል። ስለዚህም ጉዳዩ ከቁጥጥሩ ውጭ ሆኖ የህዝብ መነጋገሪያ እንዲሆን አይፈልግም። ያ ሆነ ማለት የተዳፈነው ፍም እሳት ፊቱ ላይ ተረጨ ማለት ነው።
ለዚህም ይመስላል በአርበኞች ግንቦት 7 የተሰነዘረበትን ጥቃት ለማብረድ ድምጹን አጥፍቶ መውተርተርን የመረጠው።
ሌላው ተጨማሪ ማስረጃ ደግሞ ወያኔ በአርበኞች ግንቦት 7 የተሰነዘረበትን ጥቃት ለመመከት ወደ አካባቢው እያሰማራ ያለው የጦር ክፍል ከአንድ ጎሳ የውጡና ቀደም ሲል በጡረታ ተሰናብተው ወያኔ ከወልቃይት ህዝብ ላይ ነጥቆ በሰጣቸው ለም መሬቶች ላይ የግብርና ስራ እያካሄዱ የሚገኙ የቀድሞ የህወሃት አባላት መሆናቸው ነው።

የአውስትራሊያና የካናዳ መንግስታት ዜጎቻቸው ወደኢትዮጵያ እንዳይጓዙ አሳሰቡ

የአውስትራሊያ መንግስት የዛሬ 15 ቀን በጋምቤላ ክልል ከ208 ሰዎች በላይ መገደላቸውንና 108 ህጻናትና ሴቶች መጠለፋቸውን ተከትሎ፣ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ማሳሰቢያ አወጣ። የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስትር በመግለጫው እንዳመለከተው፣ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ለማድረግ እቅድ ያላቸው አውስትራሊያውያን ለጉዞ ከመዘጋጀታቸው በፊት የጉዞውን አስፈላጊነት መመርመር እንደሚገባቸው ገልጿል።
የአልሻባብ አሸባሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የመንግስት ህንጻዎች፣ ታሪካዊ ቦታዎችና የውጭ ዜጎች በሚያዘወትሩባቸው ስፍራዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን መረጃ እንደደረሰውም የአውስትራሊያ መንግስት የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው በዚሁ መግለጫ አስታውቋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በማንኛውም ሰዓት ሊደርስ የሚችለውን የሽብርተኝነት ጥቃት በመገንዘብ የአውስትራሊያ ዜጎች ወደኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ማሳሰቡ በዚሁ ትናንት በወጣው ማሳሰቢያ ላይ ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ከማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ሲደረግ የቆየው ተቃውሞ በማንኛውም ሰዓት ሊያገረሽ ስለሚችልና በአካባቢውም አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ባለመኖሩ አውስትራላውያን ወደኦሮሚያ ክልልና አካባቢው እንዳይጓዙ በማሳሰብ፣ ዜጎቹ ተቃውሞ ወደሚካሄድባቸው ስፍራዎች እንዳይጓዙ የአውስትራሊያ መንግስት የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው በዚሁ መግለጫ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም በሚደረጉ ታላላቅ ስብሰባዎችን ዜጎቹ እንዳይሳተፉ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ የሚጓዙበት አካባቢ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ማረጋገጫ ካላገኙ አደጋ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
በተለይም በአዲስ አበባ የመርካቶ አካባቢ፣ የሱማሌ ክልልና ድንበር አካባቢዎች፣ የኤርትራና ሱዳን ድንበር አካባቢዎች፣ የኬንያና የደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢዎች፣ የጋምቤላ፣ በአፋር ክልሎች፣ የጸጥታ ችግር ያለባቸው በመሆናቸው ዜጎቹ በተጠቀሱት አካባቢዎች እንዳይጓዙ የአውስትራሊያ መንግስት የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የካናዳ መንግስት በኤርትራ፣ በሱማሌ፣በኬንያ፣ በሱዳና ደቡብ ሱዳን የድንበር አካባቢዎች ዜጎቹ እንዳይጓዙ ጠቅሶ፣በጋምቤላ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል በአምቦ አካባቢም ዜጎቹ እንዳይጓዙ አሳስቧል።

የስራ ማቆም አድማና የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የጠየቁ የደሴ መምህራን እየተዋከቡ ነው ።

ሚያዚያ 14፣ 2008 ዓም የደሴ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር አጠቃላይ 3ኛ ጉባኤ ተደርጓል። በስብሰባው ላይ የ33 ትምህርት ቤቶች የመሰረታዊ መምህራን ማህበር አመራሮች፣ የደሴ ከተማ ብአዴን ተወካይ፣ የትምህርት መምሪያ ሃላፊና የደህንነት ሰዎች ተገኝተዋል። የስብሰባው አጀንዳ የመምህራን ማህበር አመራሮችን ምርጫ ለማካሄድ ቢሆንም፣ ስብሰባው እንደተጀመረ መምህራን አሁን ስብሰባ ለማካሄድ አንችልም የሚል ተቃውሞ አሰምተዋል። የመምህራን መሰረታዊ ማህበራት አመራሮች ፣ “እኛ ከዚህ በሁዋላ ምርጫ አንፈልግም፣ ኢህአዴግ 25 አመታትን ገዝቷል፣ በቃው፣ ለውጥ አላየንም፣ ልማትና እድገት የለም፣ እኛ በረሃብ እየተሰቃየን ነው ፣ ማህበራችንን ማዋቀር አንፈልግም፣ ከፖለቲካ ነጻ አይደለም” ያሉ ሲሆን፣በተለይ መምህራን የትምህርት ጥራት እናስጠብቃለን እያልን ባለንበት ወቅት ትምህራታቸውን ያላጠናቀቁ መምህራን እየተመደቡ ዜጎቻችንን እያበላሹ በመሆኑ፣ ይህንንም እየተቃወምን ስለሆነ ህገመንግስታዊ መብታችንን ለማስጠበቅ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደምናደርግ እናሳውቃለን ብለዋል። መምህራኑ ተቃውሞአቸውን ካቀረቡ በሁዋላ፣ በታዛቢነት የተገኙት የብአዴን ተወካይ፣ የትምህርት መምሪያ፣ የትምህርት መምሪያ ምክትል ሃላፊና ካድሬዎች የመምህሩን መብት በማፈንና በማስፈራራት ስብሰባውን እነሱ በሚፈልጉት መልኩ ለማስኬድ ጥረዋል። ባለስልጣናቱ ከፉከራ የዘለለ የምታመጡት የለም እንዳሉዋቸው የሚናገሩት መምህራን፣ ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ የስራ ማቆም አድማ ማድረግ እንደማይችሉ ተናግረዋል። ከስብሰባው በሁዋላ አንድ የሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቤት የስራ ማቆም አድማ እንደሚያደርግ በመግለጽ ጽሁፍ ማቅረቡንም መምህራን ተናግረዋል። ይህን ተከትሎም በደሴ የጸጥታ ሃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተመድበው ቅኝት በማድረግ ላይ ናቸው ፡፡ መምህራን ከኑኖረና ከአስተዳደር በደል ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ላይ ሲሆኑ፣ መንግስት የጥያቄው መግፋት እያሳሰበው መምጣቱን ተከትሎ በቅርቡ ለመምህራን የቤትና የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያመቻች ገልጿል።

Daniel Mulatu's photo.

የከሸፈው የበአዴን/ህወሃት/ኢህአዴግ ስብሰባ በዳላስ!

ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ April 24, 2016 ወያኔ/ኢህአዴግ ጠፍጥፎ የሰራው የበአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት ከክልሉ ተወላጆች ጋር በልማት ዙርያ እወያያለሁ በሚል የዘወትር ዲስኩራቸው ለማሰማት ወደ ዳላስ/ቴክሳስ መምጣታቸውና ስብሰባ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ስብሰባው በበአዴን የዳላስ ተወካዮችና በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኢንባሲ የተዘጋጀ ነው ቢባልም ከመግቢያው በር ጀምሮ ተቆጣጣሪ የነበሩት የህወሃት/ኢህአዴግ ሰዎች ነበሩ። የክልሉ ተወላጆች ጨምሮ አያሌ ኢትዮጵያውያን ወደ ስብሰባው ስፍራ ቢያመሩም የመግቢያ ቲኬት የላችሁም በሚል ወደ አዳራሹ እንዳይገቡ ታግደዋል።
የስብሰባው አዳራሽ ባዶ እንዳይሆንባቸው የህወሃት/ኢህአዴግ አባላት የተገኙ ሲሆን በቅጡ ተቆጥረው በአጠቃላይ ከ45 አይበልጡም ነበር። ከ50,000 በላይ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት ዳላስ ከተማ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣን መጥቶ ትንሽ ቁጥር ያለው ህዝብ ስብሰባው ላይ መሳተፉ የዳላስ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምን ያክል በወያኔ ተስፋ የቆረጡና የተማረሩ መሆናቸውን ነው።
ስብሰባው ላይ ከተሳተፉትና ካዘጋጁት ውስጥ ተኮላ፣ ፀሃይጽድቅ፣ ኢብራሂም፣ ሙሉጎጃም ገዳሙ፣ አቶ መሰረት፣ ወ/ሮ መሰረት፣ አያሌው አርጋው፣ ወ/ሮ አለምፀሃይና ሌሎችም ይገኙበታል። ሰው በላ የሆነውን አንባገነኑና ፋሽስቱ የወያኔ/ኢህአዴግ ስርዓትን እድሜ ለማራዘም በታማኝነት ተግተው የሚሰሩት እንዚህ ጥቂት አደርባዮች ለይቶ በማወቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። አብዛኛዎቹ በኮሚኒቲያችን፣ በቤተክርስቲያን፣ ኢትዮጵያዊ በሆኑ የሲቪክ ማህበራት ውስጥ እራሳቸው ሸሽገው የወያኔ 52 ገፅ የዲያስፖራ ፖሊሲ ለማስፈፀም የስለላ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
እነዚህ ተላላኪ የወያኔ ተኩላዎችን ለይቶ በማወቅ እራሳችን እንጠብቅ፤ ለሌሎችም እናሳውቅ። ለሆዱ ያደረ ባንዳ ዘመድና ጓደኛው ሆዱና ሆዱ ብቻ ነውና!
የነፃነት ቀን እሩቅ አይደለም!
በፅናት እንታገል!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አዲሱ ትውልድ የኢትዮጵያን አንድነት እንዲጠብቅና የታሪክ ህፀፆችን እንዲያርም ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ አንድነት የመጠበቅና የታሪክ ህፀፆችን ማረም ከአዲሱ ዘመንት ዲሞራቶች ይጠበቃል ሲል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ገለጸ። ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ የዘንድሮ ግንቦት 20” በሚል ርዕስ ሰሞኑን ከወህኒ ቤት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው ፅሁፍ ኢህአዴግ ወደስልጣን የመጣበትን 25ኛ አመት በማስመልከት ያለፉትን 50 አመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ በመገምገም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።
በኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ውስጥ የነበረው የሃይል አሰላለፍ እንዲሁም በህብረ-ብሄርና በብሄር ፓርቲዎች መካክል የነበረውን ልዩነት በመዘርዘር ለኢትዮጵያ ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅ ጥሪ አቅርቧል።
“ተማሪዎች እንቅስቃሴያቸውን ከጀመሩ ከ55 ዓመታት በኋላም የዮሃንስና የምኒሊክ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ የፈጠረው ሽኩቻ የኢህአዴግ ቅኝት ጸረ-ዲሞክራሲ እንዲሆን ምክንያት ከሆኑት ግብዓቶች መካከል አንዱ ሆኖ ይገኛል ያለው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሲያጠቃልልም “የታሪክ ጣጣ የኦሮሞና የሶማሌ ብሄርተኞችን ነፍስ ዕረፍት እየነሳ ነው፥ የታሪክ ህፀጾች የማይቀበሉ ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ ሃይሎችም አሉ፥ ይህ ሁሉ ተደማምሮ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው፣ መፍትሄውም ከአዲሱ ዘመን ዲሞክራቶች ይጠበቃል” በማለት ለሃገሪቱ ችግር ዕውነተኛና ዘላቂ መፍትሄ እንደሚጠበቅ ጥሪ አቅርቧል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከመስከረም ወር 2004 ጀምሮ በአሸባሪነት ተከሶ በወህኒ ቤት የሚገኝ ሲሆን፣ የ18 ዓመታት እስር እንደተፈረደበት ይታወቃል። ክሱም ሆነ ፍርዱ እውነትም ሆነ ህጋዊ መሰረት እንደሌለው ለማመልከት ወይንም በፖለቲካ አመለካከቱ መታሰሩን ለማስረዳት በጽሁፉ ግርጌ “የህሊና እስረኞች” ሲል አስፍሯል።

 
Follow

Get every new post delivered to your Inbox.

Join 19,663 other followers

%d bloggers like this: