በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት ኃላፊዎችና ባለሀብቶች ቁጥር 53 ደረሰ

ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ በሕዝብና በመንግሥት ሀብት ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ በስኳር ኮርፖሬሽን የመስኖና ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታና ሀዚ አይ አይ ደረጃ አንድ ጠቅላላ ተቋራጭ ባለቤት አቶ ዛኪር መሐመድ ናቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ምን ያህል በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡

አቶ ዓለማየሁ ጉጆ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አሠራሩን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያዘረጋውን ቴክኖሎጂ መመርያንና ደንብን መሠረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣት ሲገባቸው፣ ለማይታወቅና በቂ ልምድ ለሌለው ድርጅት በመስጠት ከ2.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም መከፈል ያልነበረበትን 280,000 ብር ሲፒኦ በማሠራት ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ ሥልጣናቸውን በመጠቀም፣ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራታቸውንም አክሏል፡፡ በፍርድ ቤቱ ያቀረበው የምርመራ ሒደት መነሻ እንጂ ሙሉ ምርመራ አለማድረጉን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ለቀሪ የምርመራ ጊዜ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

አቶ ዓለማየሁ በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት፣ በተጠረጠሩበት ጉዳይ የተደራጀ መረጃ በመሥሪያ ቤቱ ይገኛል፡፡ በእሳቸው ግምት እስከተያዙበት ባለው ጊዜ ውስጥ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን እያጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸው፣ ታስረው የሚገኙበት ክፍል ውስጥ 20 ሰዎች በመኖራቸው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡ የስኳራቸው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ አሥጊ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከተያዙ ቀን ጀምሮ ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ማንንም ሰው ማግኘት ባለመቻላቸው፣ በቂና አስተማማኝ ዋስ ጠርተው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ለተለያዩ ተቋራጮች የተሰጡ አምስት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዲዛይኖችን በማሠራት፣ የኮንትራት ጊዜያቸውን ባለመጥቀስ፣ የግንባታ ጊዜ በማራዘምና ከኮንትራክተሮች ጋር በመመሳጠር በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቶ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናትን ጠይቋል፡፡

አቶ ዛይድ በጠበቃቸው በኩል ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ መርማሪ ቡድኑ የገለጸው በሰነድ የሚታይ በመሆኑ የጠየቀው 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተገቢ አይደለም፡፡ አቶ ዛይድ ባለሥልጣኑን ከለቀቁ ሁለት ዓመት እንዳለፋቸውና መንግሥት ከአገር ውጭ ለሥራ መድቧቸው እየሠሩ መሆናቸውን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽኑ አቶ ኪሮስ ደስታ ደግሞ የመስኖና ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ፣ ለጣና በለስ ፕሮጀክት ቧንቧ ግዥ በጨረታ ከቀረበው ዋጋ በላይ ለሦስት ጊዜያት 2,983,396 ብር፣ 131,554,000 ብር እና 49,559,992 ብር ግዢ እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ድርጅት 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት በመስጠት በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

አቶ ኪሮስ በሰጡት ምላሽ ድርጅቱን ከለቀቁ ሁለት ዓመት እንዳለፋቸው ተናግረዋል፡፡ ከቤታቸውም ሆነ ከመሥሪያ ቤቱ ሁሉም ዶክመንቶች የተወሰዱ መሆኑን በመግለጽ፣ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ አይደለም ሲሉም ተቃውመዋል፡፡

ልጃቸው ዩኒቨርሲቲ ስለምትገባ በስልክ አግኝተው እንዲያነጋግሯት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡ ቀደም ብሎ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውለው በታሰሩት እነ ካሣይ ካቻ መዝገብ የተካተቱት የሀዚ አይ አይ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጭ ባለቤት አቶ ዛኪር መሐመድ ግምቱ 3,315,200 ብር የሆነ 500 በርሜል አስፋልት በውሰት ወስደው አለመመለሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ አቶ ዛኪር በሁለት ወራት ውስጥ ለመመለስ የተዋሱትን አስፋልት፣ ከኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ሳይመልሱ መቅረታቸውንና ከላይ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ያህል ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡

አቶ ዛኪር በሰጡት ምላሽ መርማሪ ቡድኑ የገለጸውን ዕዳ መክፈላቸውን ገልጸው፣ ተጨማሪ 14 ቀናት ሊፈቀድ አይገባም ብለዋል፡፡ የዋስትና መብታቸውም እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክርክሩን ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ የሁሉንም ተጠርጣሪዎች የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡ አቶ ዛኪር ቀደም ብለው ፍርድ ቤት ከቀረቡት ጋር ነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ በማለት የአሥር ቀናት ጊዜ ፈቅዷል፡፡ በአቶ ዓለማየሁ፣ በአቶ ኪሮስና በአቶ ዛይድ ላይ የቀረበውን የ14 ቀናት ጊዜ በመፍቀድ ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቤተሰብ፣ በሕግ ባለሙያና በሃይማኖት አባት የመጎብኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ የፌዴራል ፖሊስ ትዕዛዙን ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡ ሕክምናን በሚመለከትም ከመንግሥት የሕክምና ቦታዎች በተጨማሪ፣ የሚፈልጉትን ሕክምና እንዲያገኙም እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡

የህወሓት መፈርከስ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያቀርባል !

በህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ የዓላማ ሳይሆን የጥቅም ግጭት ተፈጠረ። ” ጅብ ሲሰርቅ ይስማማል ሲካፈል ነው የሚጣላው ” እንደ ሚባለው ሰሞኑን የህወኃት/ኢህአዴግ ሰዎች በማን አለበኝነት ለ26 ዓመት እነሱ እና መሰሎቻቸው የዚችን ምስኪን አገር ሀብትና ንብረቷን በመዝረፍ እነሱ እንደሚሉት በእድገት ጎዳና ያለች አገር ሳትሆን እጅግ ኃላ ቀር ከሚባሉ አገሮች የአገር ጭራ አድርገዋት ትገኛለች።

በመሆኑም ይህ ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የተዘፈቀና አገሪቱን ለከፋ ድህነት ከመዳረጉም በላይ ለዕዳ ዳርገዋት ይገኛሉ። ይህን አገራዊ ችግር የተናገሩ ሙሁራን፣የፖለቲካ ሰዎች፣የራሳቸው አባል የሆኑ ሳይቀር ተገድለዋል ፣ታስረዋል፣ከአገር በግፍ ተሰደዋል።

ከዚያም ጉዳዩ ይህ ስርዓት በስልጣን ላይ ካለ ሙስናን መከላከልም ሆነ ዘራፌዎችን በህግ ለመጠየቅ የማይቻል በመሆኑ በሁሉም መልኩ የተዘጉትን መንገዶች ማለትም የዴሞክራሲ( የፖለቲካ)፣የኢኮኖሚ፣የማህበራዊ መብቶችን ማስፈን የሚቻለው በኃይል እንጅ በሰላማዊ ወይም በልመና እንዳልሆነ ያመኑ የትጥቅ ትግልን በአማራጭነት በመያዝ በአሁኑ ሰዓት ስርዓቱን ለከፋ ችግር እንዲወድቅና በርካታዎቹን ከጎናቸው በማሰለፍ ለህዝብ አሊንታና መኩሪያ ለጠላት ደግሞ ድንጋጤና ፍርሃትን ለቆበት ይገኛል።

በሌላ በኩል የራሱ የስርዓቱ ሰዎችም ቢሆኑ ሙስናን፣ስልጣንን ያላግባብ መጠቀምን፣ በተለያዩ ፕርጀክቶች ስም የተመደበን ገንዘብ መዝረፍ ይቁም ማለትና መጠየቅ በራስ ላይ እንደመፍረድ የተቆጠረ ሆነ ፣ ከዚያም ዝርፊያውን በጋራ ተያያዙት ከዚህ ላይ ግን ግጭቶች ብቅ አሉ እሱም ቁልፍ እና በርካታ ገንዘብ የሚዘረፍባቸውን ቦታዎች እኔ ልያዝ እኔ ልያዝ በሚል፣ከዚያም ህወኃት ያለውን ጡንቻ በመጠቀም ቦታዎችን ጠቅልሎ ያዘ ከዚያም ከፍተኛ ገንዘብ የሚመደብላቸው ድርጅቶችን መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ሜቴክን መሰረቱ በዚህ ድርጅት አማካኝነት አገሪቱ እንዴት በዘራፊዎች እየተቦጠቦጠች እንደሆነ ሁላችንም እያየን ነው።

ከዚያም ህዝቦች ኧረ ባካቹህ ሙስና የስርዓቱ መገለጫ ሆነ፣ህዝብ ድህነት አጠቃው፣ ጥቂቶች እጅግ በለፀጉ ብሎ ሲጠይቅ ለተወሰነ መልስ ወይም ማስታገሻ ይሆን ዘንድ ምስኪኑን የበታች ሰራተኛ ሰብስቦ በማሰር በራሱ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ” ሙሰኞችን በቁጥጥር ስር አዋልናቸው” እያለ ይለፈልፋል ይህን የሰሙ አንድ አዛውንት አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን በሚመሩት የህዝብ መድረክ ላይ የሚከተለውን ቃል ተናገሩ
” አንድ ሰው መንገድ ወጥቶ እየሄደ ሳለ ይመሽበትና ከእንድ ቤት አሳድሩኝ ብሎ ይገባል ሰዎችም እሽ ብለው የመሸበትን እንግዳ ተቀብለው ወደ ቤት አስገቡት በቤቱ ባል ሚስትና አንድ ልጅ ብቻ ይኖራሉ፣ ከዚያም ራት እየተበላ በጫወታ ላይ ድንገት ሚስት ያመልጣቸዋል ከዚያም ደንገጥ አሉ እና አንተ ልጅ ብለው ከእንግዳ ፊት እንዴት እንዴህ ታደርጋለህ ብለው ልጅን በኩርኩም ይመቱቷል፣ ከዚያም ትንሽ ይቆይና ባል ድንገት ያመልጣቸዋል እሳቸውም ደንገጥ በማለት አሁንም ልጃቸውን አንተ ባለጊ በማለት በኩርኩም ይመቱታል ከዚያም ጫወታው ያልቅና እንግዳው ከመቀመጫቸው ሲነሱ እሳቸውም ያመልጣቸዋል ሰውየው ደንገጥ ብለው የት አለ ያነ የፈረደበት ልጅ በሉ አምጡትና እኔም በኩርኩም ልበለው አሉ” በማለት ተረቱባቸው የናንተም የሙስናው ትግል እንዲህ ነው አሏቸው።

እንግዲህ በአገሪቱ ያለው የሙስና ሁኔታ ከህዝብ የተደበቀ እንዳልሆነና ሙሰኞች እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ ያውቃል ስለሆነም ይህን ህዝብ ማታለል የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል ህወሓት/ ኢህአዴግ በሚከተሉት ነገሮች አጣብቅኝ ውስጥ ገብቷል።
1ኛ፣ ጂቲፒ እያለ በየ አምስት ዓመት የሚያቅዳቸው እቅዶች ከወረቀት አልፈው ጠብ የሚል ነገር አላሳዩም ይባስብለው ህዝብን በማፈናቀል እና አገሪቱን ለዕዳ ከመዳረግ ያለፈ የፈየዱት አለመኖሩ
2ኛ፣ስርዓቱ ከዓመት ዓመት እየወረደና በተለይ በአሁኑ ሰዓት በነፃነት ታጋዬች በሁሉም ዘርፍ ( በትጥቅም ትግል፣በዲፕሎማሲ) መወጠሩ በስርዓቱ አገልጋዬች ላይ ለፍተኛ ስጋት በመደቀኑ እነዚህም ህዝቡ ቃል የገባንለት ነገር ባለማሳካታችን በጥያቄ እያስጨነቀን ነው የሚሉና እኛ ምንም ሀብት ሳንይዝ ሊሎች በዘረፉት የነሱ አገልጋይ ሁነን ነገ ልንጠየቅ ነው ስለዚህ ከአለንበት ከክልል ኃላፊነት ወደ ላይ አውጡን ወይም አባሳደር አድርጋቹሁ ሹሙን የሚል ጥያቄ በብዛት መምጣት ጀምራል።

በተለይ ለዛሬ መነሻ የሆነን በአገሪቱ የስኳር አቅርቦትን ይፈታሉ የተባሉ ፉብሪካዎች በልዩ መልኩ አደረጃጀትና አመራር ተመድቦላቸው የነበሩ ፉብሪካዎች የውሃ ሽታ መሆናቸውና የተበላው ገንዘብ ደግሞ የትየለሌ መሆኑ ከፍተኛ መነጋገሪያ ከሆነ ውሎ አድራል ወያኔም ለጥያቄው ቅድም አንድ አባት እዳሉት ዋናዎቹ መሪዎች እነ አባይ ፀሀዪ ተቀምጠው ታችኞችን ማሰሩ መፍቴሄ አለመሆኑ እውነታው እየተገለፀ መጥቶ በአሁኑ ሳዓት የነአባይ ፀሀዪ ቡድን እና የሌሎቹ ቡድኖች ትንቅንቅ ውስጥ ገብተዋል።

በመሆኑም ይህ የበሰበሰ ስርዓት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል በተለይ ሙስና መገለጫ የሆነበት” በሙስና የተጨማለቀ ስርዓት በሁለት ጎን ይወጠራል ይህም ሙስናን ልዋጋው ቢል ስርዓቱ ይፈርሳል፣ሙስናን ዝም ብሎ ቢመለከትም ይፈርሳል” ስለዚህ ይህ ስርዓት ፈራሽ መሆኑን አውቀን ግብዓተ መሪቱን የማፉጠን ስራ ከሚሰሩት የነፃነት ታጋዬች ጎን እድንሰለፍ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ።

በእስር የሚገኙ የኦፌኮ መሪዎች የአውራ ፓርቲ አስተሳሰቦች ለቀው አዲስ ስርዓት እንዲፈጠር መግለጫ አወጡ

በእስር ቤት የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ/ ኦፌኮ/ መሪዎች የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የልማታዊ መንግስትና የአውራ ፓርቲ አስተሳሰቦች ቦታ ለቀው አዲስ ሥርዓት እንዲፈጠር በመጠየቅ መግለጫ አወጡ።
የድርጅቱን ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የኦፌኮን መሪዎች አሁን በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በተሐድሶ ስም የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተግባራዊ የማይሆንና ሕዝብን ለመደለል የሚደረግ ሙከራ ነው ብለዋል።
እስረኞቹ “በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ አይጨመርም” በሚል ያወጡት መግለጫ እንደሚያመለክተው ጥልቅ ተሐድሶ በሚል በገዥው ፓርቲ የሚሰበከው አስተሳሰብ ተግባራዊ ሊሆን የማይችልና የነበረውን የሚደግም እንቅስቃሴ ነው ብለዋል።
የሀገሪቱ ተቋማት ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዋና ኦዲተር፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የፀረ ሙስና እንዲሁም የእንባ ተቋማት ጠባቂ መስሪያ ቤቶች አደረጃጀታቸውና አፈጣጠራቸው በኢህአዴግ አስተሳስብ የቃኙ በመሆኑም ፋይዳ የላቸውም ብሏል መግለጫው።
ተቃዋሚዎችን በገፍ በማሰርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገጉ የሕዝብን እንቅስቃሴ ማፈን እንደማይቻልም በእስር ቤት የሚገኙ የኦፌኮ አመራሮች በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ባለፉት 26 የአገዛዝ ዓመታት ሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ የኢኮኖሚ ዘረፋና የፖለቲካ ጭቆና የተፈፀመ መሆኑንም መግለጫው አስታውሷል።
በተለይ ደግሞ ከሕዝብ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ በተወሰደው የኃይል እርምጃ አገዛዙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደሞቱ እንዲታሰሩ እና ከፍተኛ ግፍና ሰቆቃ እንዲፈፀምባቸው አድርጓልም ብለዋል።
በጥልቅ ተሐድሶ ስም የሚስተካከል ነገር ስለማይኖር በስልጣን ላይ ያለው አምባገነን መንግስት ስለተቀየረ መፍትሄ እንደማይኖርና ትግሉም እንደሚቀጥል መግለጫው አሳስቧል።
በሽብርተኝነትና አመፀ በመቀስቀስ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት የኦፌኮ አመራሮች ጉዳያቸው በፍርዱ ሂደት ላይ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በቀጠሮ መራዘም ምክንያት ውሳኔ እንዳላገኙ ይታወቃል።

አንድ የአርበኞች ግንቦት 7 የአዲስ አበባ ህዋስ የህወሓትን የድብቅ ማሰቃያ ቦታ እና የመሣሪያ ማከማቻ አወደመ።

ቅዳሜ ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም አንድ የአርበኞች ግንቦት 7 የአዲስ አበባ ህዋስ አዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ከቀድሞ ናዝሬት አውቶቡስ ተራ አጠገብ የሚገኘውን የህወሓትን የድብቅ ማሰቃያ ቦታ እና የመሣሪያ ማከማቻ አወደመ። ቦታው ቀደም ባሉ ዓመታት የጉምሩክ መጋዘን ሆኖ ያገለግል ነበር። በቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቦታው የሚያገለግለው በፌደራል ፓሊስ የመሣሪያ ግምጃ ቤትነትና በስውር ማሰቃያነት ነው።


በርካታ ወገኖቻችን ዓይኖቻቸው እየታሰሩ ወደዚህ ቦታ እየተወሰዱ ስቃይ (ቶርቸር) እንዲደርስባቸው በመደረጉ ለዘላቂ የአካልና የስነልቦና ጉዳት ተዳርገዋል። በዚህ ግቢ ውስጥ በደረሰባቸው ስቃይ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖችም አሉ። በዚህ ግቢ ውስጥ በርካታ ወንድና ሴት እስረኞች እጅግ አሰቃቂና ኢሰብዓዊ በደል ተፈጽሞባቸዋል። በዚህ ግቢ ውስጥ በደሰረባቸው ስቃይ ምክንያት ዘር ማፍራት እንዳይችሉ የተደረጉ ወገኖቻችን በርካቶች ናቸው። በዚህ ፀረ ትውልድ እና ፀረ ኢትዮጵያ ተቋም ላይ ነው የአርበኞች ግንቦት 7 ህዋስ እርምጃ የወሰደው።


በተወሰደው ጥንቃቄ የተሞላበትና የተጠና እርምጃ ሳቢያ በግቢው ውስጥ የነበሩ መጋዘኞች ከነመሣርያዎቻቸው በእሳት እንዲጋዩ ተደርጓል፤ በተወሰደው እርምጃ ሳቢያ የተቀሰው እሳት በሁለት ሰዓታት ያህል ማጥፋት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ የተወሰደውን እርምጃ በዓይኖቹ እንዲያይና በህወሓት አምባገነን አገዛዝ የሚደርስበት ስቃይ ቁጭት እንዲወጣ እድል ፈጥሯል።

በተወሰደው እርምጃም አገር ወዳድ የፌደራል ፓሊስ አባላት የህቡዕ እርዳታ አድርገዋል።
ለወደፊቱም ተመሳሳይ እርጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ የአርበኞች ግንቦት 7 የአገር ውስጥ ህቡዕ አመራር ገልጿል። በተጨማሪም እያንዳንዱ አገሩንና ነፃነቱን የሚወድ ዜጋ በየተሰማረበት መስክ ሥርዓቱን የሚያዳክሙ የሕዝባዊ እምቢተኝነትና የሕዝባዊ አሻጥር እርምጃዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስቧል።
ድል ከእኛ ነች እናሸንፋለን!!

የአቋም መግለጫ:- የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ በሲያትል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ በሲያትል
Ethiopian National Unity Convention in Seattle

May 27 & 28, 2017

Ethiopian Community Hall
8323 Rainier Ave S, Seattle, WA 98118

የአቋም መግለጫ

ይህ በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነውና አሜሪካ ውስጥ በዋሽንግተን ስቴት ሲያትል ከተማ ግንቦት 19 እና 20 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ጉባኤ ላይ ከመላው ዓለም የመጡ ከ20 በላይ ታዋቂ ምሁራን፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሲቪክ ማህበራት መሪዎች፣ እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል። በሲያትል እና ዙሪያዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአካል ተገኝተው በጉባኤው የተሳተፉ ሲሆን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በመላው ዓለም የሚገኙ ወገኖቻችን ደግሞ በኢሳትና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች ውይይቱን ተከታትለዋል።

በሲያትል የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ ተሳታፊውች የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታዎች ገምግመንና በሀገራችን ብሄራዊ አንድነት፣ የጋራ ራዕይና ሀገራዊ አጀንዳችን ላይ ሰፊ ውይይት አካሄደን የሚከተለዉን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ ዛሬ ግንቦት 20 2009 ዓ.ም. አውጥተናል፡፡

1. በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተከትሎ በንጹሃን ዜጎች ላይ በወያኔ ልዩ ጦር ኃይል የተወሰዱትንና እየተወሰዱ ያሉትን እጅግ ዘግናኝ አረመኔያዊ ጭፍጨፋዎችንና አፈናዎችን አምርረን እናወግዛለን፤ ይህንን ግፍ የፈጸሙ አካላት በሙሉ በሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

2. ወያኔ/ኢህአዴግ ለተለየ አመለካከት ቦታ የማይሰጥ፤ በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተውና አማራጭ ፖሊሲዎች ይዘው የሚታገሉ ኃይሎችን በፀረ ሕዝብነት የሚፈርጅ፤ ለዜጎች መብት መከበር ፍፁም ደንታ የሌለው አምባገነናዊ ስርአትን የሚከተል ስለሆነ በየጊዜው በዜግነታቸዉ ሊኖራቸው የሚገባውን መብት በሰላማዊ መንገድ ስለጠየቁ ብቻ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች በየእስርቤቱ እንዲማቅቁ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በየቦታው ታስረው የሚገኙ የህሊና እስረኞች ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ አጥብቀን እንጠይቃለን፤ ለተግባራዊነቱም በፅናት ለመታገል ቃል እንገባለን፡፡

3. ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ታሪክና የስብጥረ-ሕዝብ ባለፀጋ ነች፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የማንነታችን መግለጫ የሆኑት ብሄር፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ሳይለያዩን ተጋብተን፣ ተዋልደን፣ ተከባብረን እና በፍቅር በደግም ሆነ በክፉ ግዜ አገራዊ አንድነታችንን ጠብቀን ኖረናል፡፡ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝብን ከህዝብ ለመነጠል፤ ተዋልደውና ተባብረው ለዘመናት የኖሩትን የሀገሪቱ ህዝቦች ለማቃቃር የሚሰሩ ኃይሎች ተደጋግመው እያታዩ ነው። ከነዚህ ኃይሎች ደግሞ ዋነኛው ሀገሪቱን በብሔርና በሀይማኖት በመከፋፈልና እርስ በርስ በማጋጨት የስልጣን ዕድሜውን እያራዘመ ያለው ወያኔ/ኢህአዴግ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሀገር ወዳድ ግለሰቦች፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ካለፈው የፖለቲካ ታሪካችን ተምረን፤ ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ላይ አተኩረን ይህን የተጋረጠብንን ብሄራዊ የመበታተን አደጋ ለመቀልበስ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንነሳ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

4. በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት መሠርቱ ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት በወያኔ/ኢህአዴግ ሲፈጸሙ የነበሩ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች፣ አስተዳደራዊ በድሎች፣ አምባገነናዊ የኃይል እርምጃዎችና ሌሎች ብሶቶች ተጠራቅመው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በአንድ ጊዜ መፈንዳታቸው ነው። በአሁኑ ወቅት የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች፣ አድሎና የፍትህ መዛባት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዜጎች በገፍ ሥራ ማጣትና መሰደድ የሀገራችን ተጨባጭ መገለጫዎች ናቸው። ስለሆነም ወያኔ/ኢህአዴግን ከስልጣን በማስወገድ ሥር-ነቀል የስርአት ለውጥ ማምጣት አማርጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብሎ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ካለው ሕዝባችን ጎን መቆማችንን እናረጋግጣለን። እኛም የበኩላችንን ለመወጣት ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ለመተባበር ቃል እንገባለን፡፡

5. ወያኔ/ኢህአዴግ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ለተቀሰቀሱ ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌለው በግልጽ አሳይቷል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ የዜጎችን የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ እና ሰላማዊ ሰልፍ እና ተቃውሞ የማድረግ መብታቸውን ከመገደቡም በላይ የመከላከያ ሰራዊቱን አሰማርቶ ዜጎችን ያስገድላል፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን በጅምላ በማጎሪያ ጣቢያዎች በማጎርና በማሰቃየት ህዝባዊ ተቃውሞዎችን መጨፍለቅን መርጧል፡፡ ይህ የወያኔ/ኢህአዴግ አምባገነናዊ ባሕሪይ በሀገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ በጥሞና የገመገመን ሲሆን ከዚህ አደገኛ ባሕሪው በአስቸኳይ ታርሞ በአሁኑ ወቅት ዘግቶ የሚገኘውን የሰላማዊ መፍትሔ በር በአስቸኳይ እንዲከፍትና ለእውነተኛ ውይይትና ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ዝግጁ እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

6. ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት ከልምድ የተማርነው ትልቅ ቁምነገር ቢኖር ካልተባበርን በስተቀር ዘረኛውና አምባገነኑን ወያኔ/ኢህአዴግን በተበታተነ ኃይል አስወግዶ ህዝብን የስልጣን ባለቤት ማድረግ እንደማይቻል ነው። በቅርቡ ወያኔ/ኢህአዴግን ብርክ ያስያዘውና በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የተካሄደው መጠነ ሰፊ ህዝባዊ እንቢተኛነትን የበለጠ ለማጠናከርና ለትግሉ የተማከለ የፖለቲካ አመራር መስጠት ያልተቻለው ጠንካራ የተቃዋሚ ኃይሎች ህብረት ባለመኖሩ ነው ብለን እናምናለን። ይህ ደግሞ ሁላችንንም የታሪክ ተጠያቂ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ስለሆነም ተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በሚያግባቧቸው ዓላማዎች ሥር በመሰባሰብ አንድ ጠንካራ ሀገር-አቀፍ የተቃዋሚ ኃይሎች ህብረት እንዲፈጥሩ፣ የተባበረ ትግል እንዲያደርጉና ለሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መሠረት እንዲጥሉ ቆመንለታል በሚሉት ህዝብ ስም እንጠይቃለን። ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በዚህ ጉባኤ የተገኘን ሁሉ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን።

7. በሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለቱ ዋነኛ ሃይማኖቶች ማለትም ክርስትናና እስልምና ለረጅም ዘመናት ሳይነጣጠሉ በሀገራችን አንድነትና በሕዝባችን ነፃነት ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ለመቋቋም፤ የሀገራችንና የሕዝባችንን አንድነትና ነፃነት ሳያደፈር እንዲቆይ ለማድረግ ያደረጉት ተጋድሎና የከፈሉት መስዋእትነት እጅግ ጉልህ መሆኑን በተደረገው ውይይት አጽንኦት ተሰጥቶታል። ወደፊትም ስለፍቅር፣ ሰላምና ተቻችሎ አብሮ ስለመኖር ከመምከር ባሻገር የሀገር አንድነት የሚጠበቀውና ዘላቂ ሠላም ማግኘት የሚቻለው ፍትህና ማህበራዊ መረጋጋት በሰፈነበት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ መኖር ሲቻል መሆኑን የሃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያስተምሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

8. ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ከሆኑት ዓበይት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የፕሬስ ነፃነት ቢሆንም በሀገራችን ኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ ፈፅሞ የለም። በተለይ የወያኔ/ኢህአዴግ የፀረ ሽብር አዋጅ ፀድቆ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ የግል ፕሬሶች ሚና እጅግ ከመገደቡም ባለፈ ሚዲያዎቹ በግዳጅ ከኢንዱስትሪው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ የመንግስት ሚዲያዎችም በሳንሱር ሰንሰለት ተሸምቅቀው ከአንድ ፓርቲ ፕሮፓጋንዳና አስተምህሮ በስተቀር ነፃ አስተሳሰቦች አይስተናገዱባቸውም። በዚህም የተነሳ ህዝቡ አማራጭ መረጃዎችን የሚያገኝባቸው ዕድሎች ሙሉ በሙሉ ተዳፍነዋል ማለት ይቻላል። የሚዲያ ነፃነት የሚረጋገጠው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን አምነን በቅድሚያ የህዝቡንና የሚዲያውን ነፃነት አፋኝ የሆነውን አምባገነን ሥርዓት አጥብቀን ለመታገል ቃል እንገባለን፡፡

9. ጉባኤው የጋራ ራዕያችን እና ሀገራዊ አጀንዳችን ምን መሆን ይገባዋል በሚለው ጥያቄ ላይ በሰፊው ከመከረ በኋላ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ዋና ዋና የጋራ ዓላማዎች አሰባሳቢ ናቸው ብሎ ያምናል፤ ስለሆነም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለው ወገናችን በነዚህ ዓላማዎች ዙሪያ ተሰባስቦ ሀገሩን ኢትዮጵያን እንዲያድን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ሀ. የጋራ ራዕያችን ብሄራዊ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ሰላም የሰፈነባትና የበለጸገች አንዲት ኢትዮጵያን ማየት ነው።

ለ. የአጭር ጊዜ ትልማችን ሀገራችን በአጭር የሽግግር ሂደት አልፋ በሕዝብ ነፃ ምርጫ ላይ ወደ ተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር ማስቻል ሲሆን

ሐ. የረጅም ጊዜ ግባችን ደግሞ ለሁላችንም የምትመች፣ ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ እውነተኛ እኩልነት፣ ፍትህና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባትና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ሀገር እንድትኖረን ማድረግ ነው።

10.በመጨረሻም ከላይ በተራ ቁጥር 9(ለ)ላይ የተጠቀሰውን የሽግግር ሂደት ሊመራ የሚችል፤ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ብሔራዊ ምክርቤት በአጭር ጊዜ ለመመሥረት የሚያስችል ጥናት የሚያደርግ፤ ከሌሎች ተመሳሳይ ጥረት ከሚያደርጉ ወገኖች ጋር በቅንጅት የሚሰራና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ ቀጣይነት ባለው መልኩ በየዓመቱ በተለያዩ ከተሞች እንዲደረግ የሚያስተባብር ቀጥሎ የተዘረዘሩት አስራ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ መስርተናል።

1. ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው
2. ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ
3. ዶ/ር አረጋዊ በርሄ
4. ዶ/ር በያን አሶባ
5. አቶ ኦባንግ ሜቶ
6. ፕ/ር ተድላ ወልደዮሀንስ
7. አቶ አበበ ገላው
8. ወ/ሮ መታሰቢያ ሙሉጌታ
9. ወ/ሮ ንግስት ሰልፉ
10. ወ/ት ርዕዮት ዓለሙ
11. ወጣት ሀብታሙ አብዲ
12. ወጣት ነጻነት ስመኝ
13. ወጣት እሸቱ ሆማ ከኖ
14. ወጣት እንዳልካቸው ጫላ
15. መምህር ልዑለቃል አካሉ
16. አቶ መንሱር ኑሩ
17. ዶ/ር አሸናፊ ጐሳዬ

ይህ ታሪካዊ ጉባኤ የተዘጋጀው በሲያትል ከተማ የሚኖሩ ሀገር ወዳዶችና በሲያትል የኢትዮዽያውያን ሕዝባዊ ፎረም በጋራ በመሆን ነው። ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተው ይህን ሀገራዊ ፋይዳ ያለውንና ወቅታዊ የሆነውን ጉባኤ እጅግ የተሳካ እንዲሆን የተሳተፉትን ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ ተሳታፊውች

ግንቦት 20 2009 ዓ.ም.
ሲያትል – አሜርካ

%d bloggers like this: