አንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል ዘመቻ ማዘጋጀቱን ይፋ አደረገ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ከህዳር 14 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ አዘጋጅቷል። በዚህ ዘመቻ ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ለልዩ ልዩ የሚዲያ ድርጅቶች በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በኩል መልዕክት በመላክ በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታና አያያዝ በተመለከተ መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፤ ከእስር እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም በመንግስት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ፓርቲው አስታውቋል። በዚህ ዘመቻ ላይ ሁሉም የዘመቻው ደጋፊና በሀገሪቱ ዴሞክራሲያው ስርዓት እንዲመሰረትና የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚሹ ሁሉ ከላይ ለተጠቀሱት ግልሰቦችና ተቋማትን ጨምሮ ሚሊዮኖች ለሚያውቁትና ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ለሚሉት ሰው ሁሉ መልዕክት በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በመላክ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ ዛሬ ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ፓርቲው ከዚህ በፊት ከህዝቢ ከፍተኛ ድፍ ያስገኘለትን “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” እና “…ለመሬት ባለቤትነት” የሚሉ የተለያዩ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ማድረጉ ይታወቃል፡፡  የዛሬውን ሙሉ ዝርዝር መግለጫ ከታች ይመልከቱ፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)

ምርጫ ሲባል አማራጭ ሳያሳጡ መሆን ይኖርበታል!!!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በሀገራችን ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ ሀገራዊ ምርጫ እንደሚደረግ በመንግስት በኩል በከፍተኛ ደረጃ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት የተከናወኑት አራት ምርጫዎች ያየን እንደሆነ በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ወደፊት ሊወስዱ እንዳልቻሉ እሙን ነው፡፡ ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፍላጎት በተለያየ መንገድ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ በተቃራኒው መንግስትና ገዢው ፓርቲ በፍፁም መለየት በሚያስቸግር ሁኔታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው ተቀናጅተው ለአንድ ለአውራ ፓርቲ ግንባታ እየሰሩ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ተግባር ምርጫን ያለ አማራጭ እንዲሆነ እያደረገው እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡

በቅርቡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዘመቻ በሚባል ደረጃ እየተካሄደ ያለው አፈናና እስር፤ ከዚህም ባሻገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ ክልከላውና ወከባው ተጠናከሮ መቀጠሉ፤ ገዥው ቡድን የምር ተቃዋሚ ፓርቲ ናቸው ብሎ የሚያስባቸው ፓርቲዎች ለማዳከምና ከምርጫው ውድድር ውጪ ለማድረግ ያለው ቁርጥ አቋም የሚያሳይ ነው። ይህ የገዢው ቡድን አካሄድ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ የሆነ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲመሰረት ፍላጎት እንደሌለው በደንብ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ የሚፈልገውን ፓርቲ እንዲመርጥ እድል ሊጠሰው ሲገባ በሥርዓቱ በእኩል ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳያካሄድ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረጉበት የሚካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ ትርጉም አልባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ የገዢው ቡድን ሀላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ በተግባር የሚደግፈው ከሠላማዊ ትግል ይልቅ የኃይልና የአመፅ መንገድ እንደሚሆን የተረዳ አይመስልም፤ ይልቁንም በሠላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ፓርቲዎች ወደ አላስፈላጊ መስመር በመግፋት ሀገራችን ወደ ብጥብጥና ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንድትገባ የሚያደርግ ሁኔታ እየተከተለ ነው የሚገኘው። በሥልጣን ላይ ያሉት ወገኖች ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በትክክል እንዳያዩ ጭፍን የሥልጣን ጥም ጋርዷቸዋል፡፡

በቀጣይ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚደረገው ምርጫም በመንግስት በኩል የመድበለ ፓርቲን ስርዓት ለማጎልበት ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከአሁኑ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመደርደር ላይ ነው። የአንድነት አመራሮችና አባላት በግፍ በማሰር ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከፍተኛ የሆነ ጫና እየተደረገ ቢሆንም አንድነት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ ህዝቡ እንዲሳተፍ በመቀስቀስና በማበረታታት የተዘጋውን የዴሞክራሲ በር በምርጫ ካርዱ ሊያስከፍት እንደሚችል ከፍተኛ እምነት አለው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደከዚህ ቀደሙ ኢህአዴግ ደጋፊዎቼ የሚላቸውን ብቻ በመራጭነት አስመዝግቦ ምርጫ የሚያደርግበት ሁኔታ ማብቃት ይኖርበታል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን በእኛ በኩል ደጋፊዎቻችን በመራጭነት እንዲመዘገቡ ከማበረታት ጀምሮ የህዝብና የፓርቲ ታዛቢ በመሆን የምርጫ ሂደቱን በሙሉ በንቃት እንዲከታተል እንዲሳተፍ የበኩላችንን ጥረት በማድረግ የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ከጅማሮው ህዝባዊ እንዲሆን ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ ይህ እርምጃም ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው የሚል እምነት አለን፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በገዥው ቡድን መልካም ፍቃድ ወይም በማንኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ የፖለቲካ ምህዳሩን እንደማይሰፋ ሊገነዘብ ይገባል። ምህዳሩ የሚሰፋውና ትክክለኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ የሚኖረው ህዝቡ በጠቅላላ ከፍርሀት ቆፈን ተላቆ በሙሉ ልብ ለመብቱ ሲቆም፣ ለፓርቲዎች ተገቢው ድጋፍ ሲሰጥ፤ ከፍ ሲልም ወደ ትግሉ ሲቀላቀል መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።

በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲ ከህዳር 14 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ አዘጋጅቷል። በዚህ ዘመቻ ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ለልዩ ልዩ የሚዲያ ድርጅቶች በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በእኩል መልዕክት በመላክ በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታና አያያዝ በተመለከተ መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፤ ከእስር እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም በመንግስት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያለመ ነው። በዚህ ዘመቻ ላይ ሚሊዮኖች ለሚያውቁትና ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ለሚሉት ሰው ሁሉ መልዕክት በኢተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በመላክ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

posted by Aseged Tamene

ከ400 በላይ ህዝብ የተፈናቀለበት መሬት በሙስና ተቸበቸበ

በደቡብ ወሎ ዞን በኮምቦልቻ ወረዳ ቀበሌ 11 በተለምዶ ጋሪሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ 470 ሰዎች ቦታው ለኢንቨስትመንት ይፈለጋል ተብሎ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ እንዲፈናቀሉ ከተደረገ በሁዋላ፣ በካሬ ሜትር 1 ብር ከ46 ሳንቲም መሬታቸው እንዲጨጥ ተደርጓል።

ጉዳዩ የህዝብ መነጋገሪያ ሆኖ ከቆየ በሁዋላ ሰሞኑን ከህዝቡ እየጨመረ የመጣውን ግፊት ተከትሎ በተደረገ ህዝባዊ ስብሰባና የካቢኔ አባላት ስብሰባ፣ የወረዳው አዛዦች ከተፈናቃዩ ደሃ ህዝብ የወሰዱትን መሬት በሙስና መቸብቸባቸውን እርስ በርስ እየተገላለጡ ይፋ አድርገዋል።

የወረዳው ላይዘን ኦፊሰር አቶ ሃብቶም የተባሉ ግለሰብ፣ አስተዳዳሪውን አቶ አበራ አበረን በአዲስ አበባና በባህርዳር መሬት ገዝተው ቤት መስራታቸውንና ቡልዶዘሮችን ገዝተው እያከራዩ መሆኑን ሲያጋልጡ፣ ምክትል ከንቲባው ደግሞ በባንክ ሂሳባቸው 8 ሚሊዮን ብር እንደተገኘባቸው እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ቤቶችን መገንባታቸውን አጋልጠዋል። አጋላጩ አቶ ሀብቶምም በከተማዋ ሁለት ቦታ ገዝተው ቤት መስራታቸውን መቀሌ ላይ ተጨማሪ ቦታ መግዛታቸው በሌሎች ባልደረቦቻቸው ተጋልጧል።

ሶስቱም ባለስልጣኖች ለጊዜው ከስራቸው ቢታገዱም እስካሁን የተወሰደባቸው እርምጃ የለም።

አንዳንድ ተፈናቃይ አርሶደአሮች ለኢሳት እንደገለጹት አቤቱታ ቢያቀርቡም ሰሚ በማጣታቸው ለስደትና ለረሃብ መዳረጋቸውን ለኢሳት ገልጸዋል ።

ሰዎቹ ከስራ ቢሰናበቱም ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረው መስራታቸው አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ከ100 በላይ አርሶደሮች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። አርሶ አደሮቹ የመሬት ዋስትና ወረቀት እንዲሰጣችሁ በነፍስ ወከፍ 4 ሺ 500 ብር ክፈሉ ተብለው የተጠየቁ ቢሆንም፣ አርሶአደሮች ግን እስከዛሬ ግብር እየከፈልን ኖረናል፣ አሁን ተጨማሪ አንከፍልም በማለት ተቃውመዋል። ይህ ተከትሎ መሬታቸውን እየተቀሙ መሬቱ ለኢንቨስተር እየተባለ እየተቸበቸበ ነው።

አብዛኞቹ ባለስልጣኖች ከኢንቨስተሮች ጋር አክሲዎን እንዳላቸው መንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። በአካባቢው የሚታየው ተደጋጋሚ ግጭት ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ።

posted by Aseged Tamene

የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን እንደማይታዘብ ታወቀ

የአውሮፓ ህብረት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በምርጫው ጉዳይ አነጋገረ

• ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ምሽቱን ያነጋግራል ተብሎ ይጠበቃል

• ህብረቱ ምርጫውን አይታዘብም ተብሏል

የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ህዳር 11/2007 ዓ.ም ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችን ያነጋገረ ሲሆን፣ በኢህአዴግ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር ምሽቱን ቀጠሮ መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአውሮፓ ህብረት የልዑል መሪ ሻንታል ሔቤሬት የተመራው የልዑካን ቡድን የሰማያዊ ፓርቲና የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትን፣ እንዲሁም የመኢአድና የመድረክን አመራሮች ማነጋገራቸው ታውቋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ሶስቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያነጋገረበት ዋነኛው አላማ ከምርጫ 2007 በፊት ያሉትን ችግሮች ለማወቅ የሚል ሲሆን በተቃዋሚዎቹ በኩል ያሉትን ችግሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል፡፡

የሰማያዊና የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል የአውሮፓ ህብረት ላቀረበው ጥያቄ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን በማመልከት፣ ‹‹የምርጫው ችግር ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ችግር የመነጨ ነው፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ሚዲያውን፣ ሲቪክ ተቋማቱንና ተቃዋሚዎችን ለማፈን መሳሪያ የሆኑ አዋጆች የአገሪቱን ፖለቲካ አበላሽተዋል፡፡ በምርጫው ላይ የተፈጠረው ችግር የዚህ ሁሉ ድምር ነው›› በማለት መሰረታዊ የአገሪቱ ችግሮች ካልተፈቱ ምርጫው ላይ የተደቀነው ችግርም ሊፈታ እንደማይችል እንደገለጹላቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአሁን ቀደም የተደረጉትን ምርጫዎች የታዘበውና በምርጫዎች ሂደት ነበሩ የተባሉትን ችግሮች በሪፖርቱ በማካተት የሚታወቀው የአውሮፓ ህብረት ስለ ምርጫው ሁኔታ በቅርቡ ስላወቀና ቀድሞ ስላልተጋበዘ ምርጫውን እንደማይታዘብ የተቃወቀ ሲሆን በአንጻሩ የአፍሪካ ህብረት ምርጫውን እንደሚታዘብ ከወዲሁ ለመረዳት ተችሏል፡፡

posted by Aseged Tamene

እነ ሀብታሙ አያሌው ዋስትና ተከለከሉ-አቃቤ ህግ ማስረጃ አሟልቶ እንዲቀርብ ታዝዟል

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው አራቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሽ በሚገኙበት የክስ መዝገብ የተከሰሱት አስሩም ተከሳሾች ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፣ ተከሳሾቹ ህገ መንግስቱን በመጥቀስ ያቀረቡትን የዋስትና መብት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የጸረ ሽብር አዋጁን በመጥቀስ ዋስትናው እንዳይፈቀድ ያቀረበውን መከራከሪያ በመቀበል የዋስትና ጥያቄውን አልተቀበለውም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ ክሱን መርምሮ በሂደት ውሳኔ እስኪያሳልፍ ድረስ በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ጠበቆች የቀረበውን ማስረጃ አለመሟላት በመመርመር አቃቤ ህግ ለህዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም ማስረጃዎችን አሟልቶ እንዲቀርብ በሚል አጭር ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በዛሬው ዕለት ተከሳሾች ከላይ ሙሉ ነጭ ሸሚዝ ለብሰው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ነጭ ማድረጋቸውም ‹ሰላማዊ ነን› የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ በማለም እንደሆነ መረዳት ተችሏል፡፡

posted by Aseged Tamene

ኢህአዴግ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ለማሰር መዘጋጀቱ ታወቀ

የኢህአዴግ አመራሮች መካከል ልዩነት ተፈጥሯል

ገዥው ፓርቲ የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችን ለማሰር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ታማኝ ምንጮች ገለጹ፡፡ ሰሞኑን የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ባደረጉት ስብሰባ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃልን ወይንስ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችን ማሰር ያዋጣል በሚል ልዩነት እንደተፈጠረ የገለጹት ምንጮቻችን በስተመጨረሻም የኢንጅነር ይልቃል መታሰር ትኩረት የሚስብ በመሆኑ ንቁ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችን ማሰር አዋጭ ነው የሚለው ቡድን ተደማጭነት እንዳገኘ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የሰማያዊና ሌሎች ፓርቲዎች አመራሮችን ‹‹ከኢሳት ጋር ግንኙነት ያደርጋሉ›› በሚል በሽብር ስም ለመክሰስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችንም ሆነ ሌሎችን ‹‹ከኢሳት ጋር ግንኙነት አላቸው›› በሚል ይከሰሳሉ የተባሉት እስከህዳር ወር መጨረሻ ሊታሰሩ ይችላሉ ሲሉ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ ስብሰባ ኢንጅነር ይልቃል ወይንም ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችን በማሰር ከተፈጠረው ልዩነት በተጨማሪ አመራሮችን በተለያዩ ሰበቦች ለማሰር በተዘጋጀውና ‹‹በዚህ መንገድ መሄዱ እስከመቼ ያዋጣናል?›› የሚሉ ጥያቄ በሚያነሱ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራሮች ልዩነት መፈጠሩንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሌሎች የፓርቲው አካሄዶች ላይ ልዩነት በመፈጠሩ ፓርቲው ውስጥ አደጋ ተፈጥሯል ያሉት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች በአቶ አባይ ፀሐዬ የሚመራ ቡድን ‹‹ልዩነታችን ቢያንስ እስከ ምርጫው ድረስ ማቻቻል አለብን›› በሚል በሁለቱ ቡድን መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት እየጣረ ነው ብለዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች 8 ፓርቲዎች ጋር በመተባበር የአዳር ሰልፍን ጨምሮ የአንድ ወር መርሃ ግብር ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን የወሩ የመጀመሪያ መርሃ ግብር የሆነው የአደባባይ ስብሰባ ለማድረግ ሲቀሰቅሱ የተገኙ የፓርቲው አራት አመራሮች መታሰራቸው ይታወቃል፡፡

posted by Aseged Tamene

Follow

Get every new post delivered to your Inbox.

Join 14,649 other followers

%d bloggers like this: