በጌታቸው ሺፈራው
ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ 13ኛ ተከሳሽ ናቸው። በአጋጣሚ ለተከሰተውና ሰባራ ሳንቲም ላልወጣበት የቂሊንጦ ቃጠሎ ማስፈፀሚያ በሚሊዮን ብር ወጭ አድርገዋል በሚል ነው የተከሰሱት። ትናንት ነሃሴ 10/2009 ዓም በመዝገቡ ላይ አራት ምስክሮች ቀርበዋል። ከአራቱ ምስክሮች መካከል አንዱ ዶክተር ተስፋዬ ያዕቆብ ይባላሉ። ዶ/ር ተስፋዬ የጥቁር አንበሳ ሀኪም የነበሩና ሰው ገድለው የታሰሩ መሆናቸውን እሳቸው ጋር አንድ ዞን ታስሮ የነበረ ወዳጄ አጫውቶኛል። ዶክተር ተስፋዬ በአተት ሰበብ ከቤተሰብ የሚገባ ምግብ ስለመከልከሉና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው ቀርበዋል።
ፍረድ ቤቱ:_ ስም?
ዶ/ር ተስፋዬ ያዕቆብ
እድሜ?
60
ስራዎት?
ሀኪም
አድራሻ?
አዲስ አበባ
ክፍለ ከተማ?
አድራሻዬን ለመንገር ፈቃደኛ አይደለሁም።
አቃቤ ህግ: እስኪ የሚያውቁትን ለችሎቱ ያስረዱልን?
መልስ:_ ነሀሴ 26/2008 አንድ ሀኪም ቂሊንጦ ውስጥ አተት ተነስቷል ብሎ አስረዳ። የቤተሰብ ምግብ አንደማይገባ ተነገረን። በጊዜው ሁሉም ታራሚ ቅሬታውን አሰምቷል። ከዛ በሁዋላ ምግብ እንዳይገባ የሚገልፀው ማስታወቂያ ተለጠፈ። ሁላችንም ፈቃደኞች አልነበርንም። የእስር ቤቱን ምግብ የማንበላ ሰዎች አለን። አተት ሊመጣ የሚችለው በተበከለ ምግብ ነው። ከውጭ የተበከለ ምግብ ይመጣል ስለተባለ የተከለከለው ለታራሚው ጥቅም ነው።
እኔ ስለበሽታው ሁኔታ ገለፃ አድርጌያለሁ። በሚዲያ( በማይክራፎን) አስተላልፍ ተብዬ ተናግሬያለሁ። በማስረዳበት ጊዜ ታራሚው አጉረመረመ። እኔ የበሽታውን መነሻና እንዴት መከላከል እንደሚቻል ነው ያስረዳሁት። ነሃሴ 28/2009ዓም ከተቆጠርን በሁዋላ እስር ቤቱ የሚያቀርበውን ቁርስ አንበላም ተባለ።……… ግርግር ተፈጠረ። ከሌላ ዞን የጥይት ድምፅ ተሰማ። እኔ ጋር የነበሩ እስረኞችን ተባራሪ ጥይት እንዳይመታቸው ቤታቸው ውስጥ እንዲቀመጡ እነግራቸው ነበር። ከሌላ ቤት እየመጡ ውጡ ወንድሞቻችን እየሞቱ ነው የሚሉ ነበሩ። አንድ በጥይት የተመታ ሰው ነበር።
በሁዋላ አበበ የሚባል ከጎንደር የመጣ መቶ አለቃ በታኝ ፖሊሶች መጥተዋል፣ ከታራሚዎች ጋር ይገጥማሉ። ችግር ይገጥመናል፣ ታራሚውን ወደ ቤቱ እንዲገባ፣ ፖሊሶችም ወደ ውስጥ እንዳይገቡ እናድርግ አለኝ። እኛም ተስማምተን፣ አረጋግተን እያንዳንዱ ሰው እቃውን ይዞ እንዲወጣ አደረግን። ( ለአቃቤ ህግ ጥያቄዎች የሰጡት መልስ ጠቅለል አድርጌ አቅርቤው ነው)
ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ( መስቀለኛ ጥያቄ):_ ከውጭ የሚመጣ ምግብ በጥንቃቄ ስለማይሰራ ነው አተት የሚያመጣው?
ዶ/ር ተስፋዬ:_ የተበከለ ምግብ ነው አተት የሚያመጣው!
ዶ/ር ፍቅሩ: እሱን አውቃለሁ! ከውጭ የሚመጣው ነው የማረሚያ ቤቱ ነው አተት ሊያመጣ የሚችለው?
ዶ/ር ተስፋዬ:_ ከውጭም ከውስጥም ይሁን የተበከለ ከሆነ ነው!
ዶ/ር ፍቅሩ: _ ገብቶኛል! ከቤተሰብ የሚገባው የተከለከለው የተበከለ ስለሆነ ነው?
ዶ/ር ተስፋዬ: ይበከላል ተብሎ ስለሚታብ!
ዶ/ር ፍቅሩ:_ አተት በተበከለ ውሃ ይመጣል ብለዋል። እስር ቤቱ የታሸገ ውሃ ያቀርባል?
ዶ/ር ተስፋዬ:_ አያቀርብም!
ዶ/ር ፍቅሩ:_ ታዲያ የእስር ቤቱ ውሃ አተት አያመጣም?
ዶ/ር ተስፋዬ:_ ይታከማል። በአጋጣሚ ካልተበከለ አያመጣም።
ዶ/ር ፍቅሩ: ያመጣል? አያመጣም?
ዶ/ር ተስፋዬ: ያመጣል ብዬ አልገምትም!
ዶ/ር ፍቅሩ: መግለጫ ሰጥቻለሁ ሲሉ ነበር!
ዶ/ር ተስፋዬ: አዎ!
ዶ/ር ፍቅሩ: ምን ስለሆኑ ነው መግለጫ የሚሰጡት?
ዶ/ር ተስፋዬ: ሀኪም ስለሆንኩ!
ዶ/ር ፍቅሩ: ተቀጥረው ነው?
ዶ/ር ተስፋዬ: እስረኛ ነኝ። የሙያ ግዴታ አለብኝ!
ዶ/ር ፍቅሩ: ማንም ሀኪም ተነስቶ መግለጫ መስጠት ይችላል?
ዶ/ር ተስፋዬ: የማረሚያ ቤቱን ህግ አላውቀውም!
ዶ/ር ፍቅሩ: ነሀሴ 26 መግለጫ ሰጥተዋል ያሏቸው ሀኪም የምን ሀኪም ናቸው?
ዶ/ር ተስፋዬ: ዶ/ር አለሙ ይባላሉ። ሀላፊ ናቸው።
ዶ/ር ፍቅሩ: የምን ሀላፊ? የቂሊንጦ ነው የቃሊቲ?
ዶ/ር ተስፋዬ: የሁሉም መሰለኝ።
ዶ/ር ፍቅሩ: አሁንም ምግብ ከውጭ እየገባ ነው፣ አሁንስ ሊበከል አይችልም?
ዶ/ር ተስፋዬ…………… (መልስ አልሰጡም)
ዶ/ር ፍቅሩ: ከውጭ የሚገባ ምግብ ማረሚያ ቤቱ ከሚያዘጋጀው በላይ የተከለ ነው?
ዶ/ር ተስፋዬ: አይመስለኝም!
ዶ/ር ፍቅሩ: በአተት ተያዙ የተባሉት ሰዎች በምን እንደታመሙ ያውቃሉ?
ዶ/ር ተስፋዬ: ስላላየሁ አተት ነው አይደለም ማለት አልችልም!
አግባው ሰጠኝ: እርስዎ የቂሊንጦን የባንቧ ውሃ ጠጥተው ያውቃሉ?
ዶ/ር ተስፋዬ: ጠጥቼ አላውቅም!
አግባው:_ ታዲያ የተበከለ ይሁን አይሁን በምን አወቁ?
ዶ/ር ተስፋዬ: ውሃ እንዴት ታክሞ ለህዝብ እንደሚደርስ አውቃለሁ።
አግባው: የእስር ቤቱ ይታከም አይታከም ያውቃሉ?
ዶ/ር ተስፋዬ: ሳይታከም ለህዝብ አይደርስም!
አግባው:_ በሚል ነው?
ዶ/ር ተስፋዬ: በሚል ሳይሆን በእርግጠኝነት!
አግባው: የቧንቧውን ውሃ በጨርቅ አጥልለን እንደምንጠጣው አያውቁም?
ዶ/ር ተስፋዬ:_ አላውቅም! ( ለግንዛቤ ያህል:_ ዶ/ር ተስፋዬና አግባው አንድ ቤት ነበሩ)
መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ : ከቃጠሎው በሁዋላ ያለው ሁኔታ ይበልጥ ለአተት አያጋልጥም?
ዶ/ር ተስፋዬ: ስለ አተት………………
መቶ አለቃ ማስረሻ: ያጋልጣል አያጋልጥም?
ዶ/ር ተስፋዬ: አጭር መልስ መስጠት አልችልም።
መቶ አለቃ ማስረሻ: ምግብ ከተከለከለበት የማረሚያ ቤቱ ሁኔታና ዝዋይ ከነበሩበት ሁኔታ የትኛው ለአተት ያጋልጣል?
ዶ/ር ተስፋዬ: ነው አይደለም የሚለውን ለመመለስ አተት ምንድን ነው የሚለውን……………
ፍርድ ቤቱ: ለተጠየቁት መስቀለኛ ጥያቄ መልስ መመለስ አለብዎት!
ዶ/ር ተስፋዬ: በማብራሪያ ነው መመለስ የምችለው!
መቶ አለቃ ማስረሻ: ዝዋይ የነበሩበት ሁኔታ ለበሽታ አያጋልጥም?
ዶ/ር ተስፋዬ: አያጋልጥም!
መቶ አለቃ ማስረሻ: ዝዋይ እያለን እጃችን ታጥበን ነበር የምንበላው?
ዶ/ር ተስፋዬ : እጃችን ታጠብን አልታጠብን፣ ባክቴሪያው ዝዋይ አልነበረም!
ፍርድ ቤቱ: ጥያቄውን ይመልሱ!
ዶ/ር ተስፋዬ: እኔ እታጠብ ነበር!
መቶ አለቃ ማስረሻ: ባክቴሪያው ዝዋይ መኖር አለመኖሩን በምን አረጋገጡ?
ዶ/ር ተስፋዬ: ቢኖር ሁሉም ይታመም ነበር!
መቶ አለቃ ማስረሻ: እኛ ወደዝዋይ ስንወሰድ ቂሊንጦ የቀሩ እስረኞች ነበሩ አይደል?
ዶ/ር ተስፋዬ: አላየሁም!
መቶ አለቃ ማስረሻ: እርስዎ 60 አመቴ ነው ብለዋል። ከእርስዎ በእድሜ ያነሱ የ20ና 30 አመት የህወሃት አባል ስለሆኑ ዞን አንድ ተለይተው እንደቀሩ አያውቁም?
ዶ/ር ተስፋዬ: አላውቅም!
ጌታቸር እሸቴ: እርስዎ ለምንድን ነው የማረሚያ ቤቱን ምግብ የማይበሉት?
ዶ/ር ተስፋዬ: ስለማይስማማኝ!
ጌታቸር እሸቴ: የማረሚያ ቤቱ ውሃ የከርሰ ምድር ውሃ መሆኑን ያውቃሉ?
ዶ/ር ተስፋዬ: አላውቅም!
ጌታቸር እሸቴ: የቂሊንጦ ውሃ ደፍርሶ አይተውት አያዉቁም?
ዶ/ር ተስፋዬ: አላውቅም!
( ለግንዛቤ ያህል! የቂሊንጦ ውሃ የከርሰ ምድር ሲሆን አሸዋ ተቀላቅሎ ስለሚመጣ እስረኛው በጨርቅ እያጠለለ ቀድቶ ነው የሚጠቀመው። ከቂሊንጦ ቃጠሎ በሁዋላ ወደ ዝዋይ የተወሰዱ እስረኞች ልብሰቸውን ተቀምተው፣ ባዶ እግራቸውን ባዶ ወለል ላይ ይተኙ ነበር። ለሳምንት ለሁለት ለሁለት ተጣምረው ታስረው ባዶ ወለል ላይ ነበር የሚተኙት። 285 እስረኛ ሁለት ሽንት ቤት ባለው አንድ ቤት ታስሮ የነበር ሲሆን ውሃ ስለሚጠፋ ምግብ የሚባላው እጁን ሳይታጠብ ነበር።)