የቤንሻንጉል ፕ/ት: ተፈናቃዮቹ ኦሮሞዎችም ናቸው – አጣርተን እርምጃ እንወስዳለን

ባለፈው ሳምንት አዲስ አድማስ ጋዜጣ በበቤንሻንጉል ክልል የሰፈሩ ዜጐች “ሕገወጥ” ተብለው እንደተባረሩ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ዜናው እንዳለው ከሆነ፡-

 በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ቦታ በማጣታቸውና የተሻለ ሥራ ፍለጋ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ ተዘዋውረው የከተሙ በርካታ ሰዎች በወረዳው ባለሥልጣናትና ፖሊሶች፤ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን…ገለፁ፡፡

የያሶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ሻምበል ዳኛ በበኩላቸው ‹‹ከየትኛውም ክልል የሚመጡ ሰዎች ለወረዳው ካላሳወቁና ካላስፈቀዱ ሕገወጥ በመሆናቸው ወደ የመጡበት እንዲመለሱ ስምምነት ላይ ደርሰናል›› ብለዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት፤ ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ ይኖሩበት ከነበረው ክልል የመሸኛ ደብዳቤ አምጥተው በያሶ ወረዳና በየቀበሌዎቹ የነዋሪነት መታወቂያ ስለተሰጣቸው ጎጆ ቀልሰው ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ (ሙሉውን እዚህ http://danielberhane.com/2013/04/03/ethiopians-amhara-benishangul-region-settlers-evicted/ያንብቡ)

ተመሳሳይ ጭብጥ ያላቸው ዘገባዎች በተለያዩ ሚዲያዎች በተለያየ አቀራረብ የቀረቡ ሲሆን፤ እንደተለመደው ኢሳት ጉዳዩን አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ 59 የተፈናቀሉ ሰዎች በጉዞ ለላይ ሞቱ ብሏል፡፡ ይሁንና የመኢአድ (የኢንጅነር ሀይሉ ሻውል ፓርቲ) ሀላፊዎች ስለሞት መረጃ እንደሌላቸው ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

በአሜሪካ ሀገር የሚገኝ በአማርኛ የሚተላለፍ የኢትዮጲያውያን ሬዲዮ (Ethio-CivilityMap of Benishangul-Gumuz Region - Ethiopiaforum) ጉዳዩን አስመልክቶ ከቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አሕመድ ናስር ጋር ቃለ-ምልልስ ከትላንት ወዲያ አድርጓል፡፡

ወደ 30 ደቂቃ ከወሰደው ቃለ-መጠይቅ ውስጥ በርዕሰ-ጉዳዩ ላይ ከሰጡት ምላሾች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ከተሞችን አስመልክቶ፡-

ከከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች ስለመኖራቸው መረጃ የላቸውም፡፡ ሊፈፀም የሚችልበት አግባብም የለም፡፡ የሀገሬው ተወላጅ በሆቴልና መሰል ንግዶች መሠማራት ባህል እንደሌለው እና ባለስልጣኖቹ ራሳቸው በመሀል ሀገር ሰዎች ንብረት በሆኑ ሆቴሎች እንደሚጠቀሙ ጠቁመዋል፡፡ ‹ችግሩ› በገጠር እንጂ በከተማ የለም ብለዋል፡፡

ገጠሩን አስመልክቶ፡-

– በክልሉ ከማጂ ዞን ባለ አንድ ወረዳ 1700 ሰዎች እንዲነሱ እንደተደረጉ መረጃ እንዳላቸው ገልፀዋል

– የሞተ ሰው የለም/መረጃ የለኝም/ ካሉ በኋላ፤ እንዲያውም ከወረዳው ባገኙት መረጃ መሠረት ተወያይተውና ሕገወጥ መሆናቸውን ተማምነው፣ ከ 20-25 ቀን ጊዜ ተሰጥቷቸው ምርታቸውን ሰብስበውና ራሳቸው መኪና ተከራይተው እንደሄዱ ነው ብለዋል

– ጉዳዩን ያስፈፀመው የወረዳው መስተዳድር መሆኑን፤ ‹ክፍተት› መኖሩን እና ሰው ልከው ማጣራታቸውንና ያም ሰው አጠናቅቆ ሐሙስ እንደተመለሰ ገልጸዋል

– በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር የአማራ ክልል <ጓዶች> መምጣታቸውን፤  አርብ መረጃ መለዋወጥና  ውይይት እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል፡፡

– የተነሱት ሰዎች አማራ ብቻ ሳይሆኑ ኦሮሞዎችም ጭምር ናቸው (ሌሎችም ብሔሮች ሊኖሩ ይችላሉ)፤ ዞኑንም የሚዋሰነው ከኦሮሚያ ክልል ጋር ነው ብለዋል፡፡

– አላግባብ የተፈፀመ ነገር ካለም ማስተካከያ እንደሚደረግ እና በአጥፊ ሀላፊዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀዋል፡፡

– በተጨማሪም ከ4 ዓመት በላይ የኖሩ፣ መታወቂያ የተሰጣቸው ሰዎች ተፈናቅለው ከሆነ እሱን  ማስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡

እንደአጠቃላይ የገጠሩን ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገሩም፡-

– ከሌላ አካባቢ ሰዎች የሚመጡበት 2 ዋነኛ መንገዶች መኖራቸውን፤ እነርሱም፡- ‹‹ጉልበት ሽጦ›› ለመኖር ተቀጥረው የሚመጡ ወይም ጫካ መንጥረው በእርሻ የሚሠማሩ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን፤

የመጀመሪዎቹን በተመለከተ መብታቸው መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጉልበቱን ሸጦ የሚኖር ካለ፤ ዛሬም ነገም ይኖራል: ከወጣም ይገባል›› ብለዋል፡፡

ሁለተኛውን ዓይነት ማለትም ‹‹ጫካ መንጥረው በእርሻ የሚሠማሩ›› ያሏቸውን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ሲጠቃለል፡-
‹‹ፖሊሲው›› የሚለው ሰፈራ በየክልሉ ውስጥ ብቻ እንደሚካሄድ፤ ክልሎች ለሰፈራ ያዘጋጁት መሬት ካለቀ እና ከክልል-ክልል ሰፈራ አስፈላጊ ከሆነ የሚመለከታቸው ክልሎች ተነጋግረው የሚያስፈጽሙት እንደሚሆን ከጠቀሱ በኋላ፤
እስካሁን በተለያየ መንገድ (ሕጋዊ ባልሆነም መንገድ) ገብተው የቆዩና በነዋሪነት የሚታወቁትን በተመለከተ የሚስተናገዱበት መንገድ እንደሚፈለግ፤ ለቀጣይ ግን ይህ ቋሚ አሠራር ሊሆን እንማይችልና እንዲያውም ማበረታታት እንደሚሆን፤ ይህም ለሰዎቹ ለራሳቸውም ለክልሉም ጥሩ እንዳልሆነ ሀገር ይወቅልን ብለዋል፡፡

——

ማስታወሻ፡- ይህ ጭማቂ ሙሉውን ቃለ-መጠይቅ ዳውንሎድ (Download) ማድረግ ለሚቸግራቸው አንባቢያን ለመርዳት፤ በችኮላ የተጻፈና ቁንጽል በመሆኑ፤ ሙሉውን ቢያዳምጡት ይመከራል፡፡

Download here (link) – የፕ/ት አሕመድ ናስር ጋር ቃለ-ምልልስ (size: 9.4 mb)

posted by Aseged Tamene

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a comment