መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዜጎች የሕገ መንግሥት ድንጋጌ እየጣሰ

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዜጎች ሊከበርላቸውና ያለምንም ችግር ተፈጻሚ ሊሆንላቸው የሚገባውን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ እየጣሰ መሆኑን፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ፡፡

የፓርቲዎቹ አመራሮች ሐሙስ ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21(2) ላይ በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ዜጎች ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸው ዕድል የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን የፓርቲዎቹ አመራሮች የታሰሩባቸውን በርካታ አባላት ለመጠየቅ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እየተመላለሱ ቢሆኑም መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙት አባላቶቻቸው በማረሚያ ቤቱ እየደረሰባቸው ባለው መንገላታት የተነሳ፣ ለከፍተኛ የጤና ችግር እየተጋለጡ መሆኑን የገለጹት የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴና  የሰማያዊ ፕሬዚዳንት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተገፍቶ መገለልና ብቸኝነት እንዲሰማቸው እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፓርቲዎቹ አመራሮች በእስር ላይ ለሚገኙ አባላት የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች በመያዝ ወደ ማረሚያ ቤቱ የሄዱ ቢሆንም፣ የጥበቃ አባላትና ኃላፊዎቹ ቁሳቁሶቹ እንዳይገቡና እነሱም መጎብኘት እንዳይችሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ፍፁም ሕገወጥ የሆነ ክልከላ የተደረገው በጥበቃዎቹ ወይም በኃላፊዎቹ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር በደብዳቤ መጠየቃቸውን የገለጹት አመራሮቹ፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ባለማግኘታቸው ድርጊቱ ሆን ተብሎ በአባሎቻቸው ላይ የአስተዳደሩ ኃላፊዎች እያደረሱት ያለ ጫና መሆኑን ለመገንዘብ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በእስር ላይ የሚገኙት አባሎቻቸው በከፍተኛ ሕመምና ስቃይ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ እንዲጎበኟቸው ቢፈልጉም፣ በተደጋጋሚ በሚደረግባቸው ሕገወጥ ክልከላ ምክንያት በአካል አግኝተዋቸው የሆኑትን ነገር መጠየቅና ማወቅ እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡

ከመኢአድ አቶ አወቀ አባተና አቶ መልካሙ ገበየሁ፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ አቶ አግባው ሰጠኝና አቶ ሉሉ መካሳ በመደብደባቸው ለሕመምና ለስቃይ የተዳረጉ ቢሆንም፣ በቂ ሕክምና ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑን ለማወቅ መቻላቸውን አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲዎቹ አባላት የሚፈልጉትን የሕግና የሞራል ድጋፍ፣ የሕክምና ዕርዳታ፣ የአልባሳትና ልዩ ልዩ አላቂ የፅዳት መገልገያዎች እንዳይቀርቡላቸው ተደርገዋል ብለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ አባላቱ ባይተዋርነት እንዲሰማቸውና ማንም እንደማያስታውሳቸው እንዲያስቡ በመንግሥት ካድሬዎች በኩል የሚደረግ ሴራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ታሳሪዎቹ ግን ለነፃነቱ የሚታገሉለት፣ የሚታሰሩለት፣ የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉለት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው እንደሚፈልጉ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡

የፓርቲዎቹ አመራሮች እየተፈጸመ ነው ያሉትን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ጥሰት በሚመለከት ሪፖርተር የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች አስተያየት እንዲሰጡ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የማረሚያ ቤቶች የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው መንግሥቴ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: