በደንቢያ ወረዳ የሚታየውን ተቃውሞ ተከትሎ አንድ ቤተክርስቲያን በወታደሮች ተቃጠለ

የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት በሰሜን ጎንደር ዞን በደንቢያ ወረዳ ጩሃይት ከተማ መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓም ጀሪ ደበርጋ ጊዮርጊስ የተባለ ቤተክርስቲያን በአካባቢው በሰፈሩ ወታደሮች ተቃጥሏል። ህዝቡ በድርጊቱ በመቆጣት ተቃውሞውን ሲያሰማ ወታደሮች ድርጊቱን የፈጸሙት የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ናቸው በማለት ህዝቡን ለማሳመን ቢሞክሩም ፣ ነዋሪዎች ግን አልተቀበሉትም።
ወታደሮቹ ድርጊቱን የፈጸሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጋዮችን በህዝብ ለማስጠላት መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።በዚህ ወረዳ በቸንከር ቀበሌ ሌሊት 9፡15 ሲሆን ንብረትነቱ የህውሐት የሆነ እስካባተር መኪና በቦንብ ተመትቷል።
በዛሬው እለት በሰራቫ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን፣ ተጨማሪ ወታደሮች ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሰዋል። ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ወታደሮችን ሲቃወም ውሎአል።
በሳምንቱ መጀመሪያ በቻይና ኩባንያ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ኮማንደር በቆየ በዛብህ፣ ጌታው ባዜ፣ መልካሙ የሚባሉ የጥበቃ ሃላፊዎች እና ሌሎችም የአስተዳደር ሃይሎች ተይዘዋል። ሰሞኑን በተፈጸመው ጥቃት 3 ሰዎች ተገድለዋል፣ 11 መኪኖችም ተቃጥለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አርበኞች ግንቦት 7 ፣ በጎንደር ቀበሌ 18 ኮሌኔል አጠና ተፈሪ በተባለው የኢህአዴግ አመራር ቤት ላይ ከሌሊቱ 10፡20 ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
ኮሎኔሉ ለህወሃት አገልጋይ በመሆን ፣ በ2008 ዓም በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ በርካታ ዜጎችን ትእዛዝ በመስጠት ያስገደለ፣ ሲሳይ ታከለ እና ሰጠኝ ባብል የተባሉ ባለሃብቶችን የገደለውን አለቃ ዮሃንስ የተባለውን የህወሃት ደህንነት ቤቱ በማስቀመጥና ከ3 ቀናት በሁዋላ አጅቦ አክሱም ማድረሱን ድርጅቱ ገልጿል።
ግለሰቡ በአሁኑ ሰዓት የማራኪ ክፍለ-ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ እና የአስተዳደርና ፀጥታ ኅላፊ በመሆን የአማራ እና የቅማንት ተወላጆችን በመከፋፈል እና እርስ በርስ በማጋጨት ስራ ላይ የተሰማራ መሆኑንም ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
በጥቃቱ የባለስልጣኑ ጠባቂዎች ላይ የመቁሰል ጉዳት መድረሱንና መኖሪያ ቤቱ በከፊል መፍሩሰን የገለጸው ድርጅቱ፣ ጥቃቱን ተከትሎ የህወሃት ደህንነቶች የአካባቢውን ነዋሪዎችን ይዘው በማሰር ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል ወታደሮችን የጫኑ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በባህርዳር ከተማ በመዟዟር በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና ለማሳደር ሙከራ አድርገዋል። ነዋሪዎች እንደገለጹት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሆን ብለው ለማጅ የሚል ምልክት በመለጠፍ በከተማው ሲዟዟሩ አርፍደዋል። ወታደራዊ ተሽርካሪዎች ከዚህ ቀደም በከተማው ወታደሮችን በመጫን ልምምድ አድርገው እንደማያውቁ የገለጹት ነዋሪዎች፣ ድርጊቱ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ይላሉ። የባህርዳር ህዝብ የልጆቹ ደም ከፈሰሰ በሁዋላ ከአገዛዙ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ መለያየቱን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ህዝቡ በአሁኑ ሰአት የሚፈልገው ለውጥ ብቻ በመሆኑ ገዢዎችን ጭንቀት ላይ ጥሏቸዋል። የዛሬው ድሪጊትም አገዛዙ በከፍተኛ ሁኔታ ጭንቀት ውስጥ እንደገባ ያሳያል ሲሉ ነዋሪዎች አክለዋል።

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: