በኢሬቻ በዓል ላይ ስለነበረው ሁኔታ አንድ የአይን እማኝ እንዲህ ይገልጸዋል

እኔና ጓደኛዬ በስልካችን ምስልና ቪዲዮ እየቀረፅን ስልምንጓዝ ጉዟችን ቀርፋፋ ነበር። በምንሄድበት መንገድ የወታደሩ ቁጥር፤ መሳሪያ የደገኑ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እጅግ ብዙ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ደንበኛ ጦር ሜዳ በሚያስመስል መልኩ በመሬት ታንክ እና በሰማይ ላይ ደግሞ የጦር አውሮፕላን ከ4:00 ሰዓት ጀምሮ በማንዠበብ ህዝብን ሲያሸብሩ ነበር። እኛም ወደ ሆረ አርሰዲ በተጠጋን ቁጥር የህዝቡ ብዛት እና የህዝብ ጥያቄ የሚያስተጋቡ ዜማዎችና መፈክሮች ጠንከር ባለ መልኩ በዚያ አካባቢ በነበሩ የበዓሉ ታዳሚዎች በሙሉ ስተጋባ ነበር። ከመፈክሮቹ በጥቂቱ።

#ነፃነት እንፈልጋለን
#ጠላታችን ወያኔ እንጂ የትኛውም ህዝብ አይደለም። ጥያቄአችን የትኛውም ህዝብ ላይ ያነጣጠረ አይደለም።
#በወያኔና ተላላኪዎቹ አንተዳደርም።
#የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም
#የአማራ ህዝብ የኮንሶ ህዝብ የሶማሌ ህዝብ የሱርማ ህዝብ የጋምቤላ ህዝብ እና ሌሎችም ወንድሞቻችን ስልሆኑ እንወዳቸዋለን
ከሁሉም ጎልቶ የሚሰማውና ሁሉም የሚቀባበልው #didnee_didnee_didnee (#እምቢ_እምቢ_እምቢ ) የሚል መፈክር ነው።

ያለመግባባቱ መንስኤና ጅምላ የዘር ፍጅቱ

ተቃውሞው ፍፁም ሰላማዊና እጅን ከጭንቅላት በላይ በማጣመር መፈክር ማሰማት ነበር። በዚሁ መሃል ኦፒዲኦ መልምሎ ያስቀመጣቸው የወያኔ ጀሌ የሆኑ አንድ የቀድሞ አባገዳ (ለገሰ?) የቱለማ አባገዳና የኦሮሚያ አባገዳዎች ሰብሳቢ በየነ ሰንበቶ እያሉ መድረኩን ተቆጣጥረው ንግግር ለማድረግ ይሞክራሉ በበዓሉ ላይ አይታይም የተባለው የፓርቲ (የኦፒዲኦ) ባንዲራም ይታያል። በዚሁ መሰረት ወጣቶች ባህላች የፓርቲ ንብረት አይደለም፤ በህዝብ የተመረጠው አባገዳ እንጂ የናንተ ተላላኪ ንግግር አያደርጉም በሚል መድረኩን በመያዝ መፈክር ማሰማት ጀመሩ። በዚህን ጊዜ ለባለስልጣኖችና ለአባገዳዎች መቀመጫ ታስቦ የተሰራው ባለ ደረጃ ጥላ/ትሪቡን ሁሉም ስላፈገፈጉ ባዶ ቀረ። በዚህን ጊዜ ወጣቶች ባዶ ቦታው ላይ መቀመጥ ይጀምራሉ። እነዚህን ልጆች ወታደሮቹ ከሌላው ህዝብ በመቁረጥና በመክበብ መደብደብና ለማሰር መጎታት ሲጀምሩ ወጣቶች በተቃውሞ ጩሀት ለመከላከል ሞከሩ። በዚህ ቅጽበት ተኩስ ተጀመረ። ከላይ ሂሊኮፕተር የጭስ መወርወር ጀመረ። መሬት ላይ ያሉትም ወታደሮች ወደ ሰው በቀጥታ ሲተኩሱ ነበር።

ራቅ ቢዬ አጥር ጥግ ጉብታ ነገር ላይ ሆኜ ወደ ፖዲየሙ ፊትለፊት እመለከታለሁ ሁኔታውንም ስከታተልና በተቻለኝ መጠን በሞባይሌ ቪዲዮ ስቀርፅ ነበር። ተኩሱ ሲጀመር ህዝቡ ወደ እኛ መሮጥ ጀመረ። መጥቼ እዚያ ጥላ ስር ስቆም ዛፎች ስር ገደል ነገር አይቼ ስለነበር ወደዚያ ላለማፈግፈግ ጥረት አደረኩኝ። ሆኖም ጥረቴ አልተሳካም ከብዙ ሰዎች ጋር ተያይዘን ገደል ገባን። ከሁሉም ከህሊናዬ በፍፁም ሊፋቅ የማይችለው ወደ ገደሉ ስንገባ አንድ በግምት ዘጠኝ ወይ አስር አመት የሚሆነው ትንሽ ልጅ አባቱ ወይኔ ልጄን ወይኔ ልጄን እያለ በሚጮህበት ሰዓት ልጁ ገደሉ አፋፍ ደርሶ ነበር። ገደሉ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል እገምታለሁ። መጨረሻውን አለማወቄ አእምሮዬን ይቆጥቁጠኛል። ወደ ገደሉ ስንገባ ብዙ ሰውሆነን ነው ተያይዘን የገባነው። ከላይም ሰው እላያችን ላይ ሲወድቅ ነበር። ገደሉ ከ ስድስት እስከ ስምንት ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን መሬት ላይ ረዘም ብሎ በዛፎች የተሸፈነ ነው። ለምን እነደዚያ እንደተቆፈረ ባላውቅም ውስጡ በጣም ይሸታል።

14570501_682571641911947_6439070365969092821_n
የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ስለነበር በኋላ ላይ እንደተከሰተው ጉድጓዱ ውስጥ ሰው ባይሞላም አጠገቤ ብቻ ወደ አምስት የማይንቀሳቀሱ ሰዎች ነበሩ። ለመሞታቸው እርግጠኛ ነኝ። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እራስን ማትረፉ የግድ ስለሆነ ገደሉ ውስጥ በእግር መቆም የቻልነው ሀረግና የዛፎች ሥር በመያዝ ወደ ላይ መውጣት ቻልን። ከገደል ስንወጣ የወጣነው ወደ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጊቢ ነበር። በጣም በሚየስደንቅ ሁኔታ ጊቢው ውስጥ የነበሩ የጊቢው ጠባቂዎች፤ የፅዳት ሠራተኞች የህንፃ ኃላፊዎች እየተቀበሉን በጭቃ የተለወስውን መላ አካላችንን ከነ ልብሳችን በአትክልት ማጠጫ የውሃ ጎማ ሲያጥቡን ነበር። በጣም ለተጎዱት የታሸገ ውሃ አምጥተው ሲያጠጡ እና አይናቸውና ጭንቅላታቸው ላይ ውሃ ሲያፈሱ ነበር። በእትክልት ማጠጫ ጎማ ከነ ልብሴ ሻወር ከወሰድኩ በኋላ ነው አንዳንድ የተላላጡ የሰውነቴን ክፍሎች ያየሁት። አይኔ በጣም እያቃጠለኝ ነበር። ጉሮሮዬ ውስጥም ያቃጥለኛል። የሚኮሰኩሰኝና የሚያቃጥለኝ አፈሩ/ጭቃውና ገደሉ ውስጥ ያለው ቆሻሻ ውሃ መስሎኝ ነበር። የጭስ ቦምቡ ጉዳይ የታወቀኝ ቆይቶ ብዙ ሰዎች ከወጡም በኋላ ተዝለፍልፈው ሲወድቁ ሳይ ነው። ልብሴ ትንሽ ጠፈፍ እንዲልልኝ ሰዎቹን ለምኜ ትንሽ ከቆየሁ በኋላ ከማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ወደ ዋናው መንገድ ወጣሁ። ያየሁት ለማመን ተቸገርኩ። ሰው በየጥጋጥጉ ተዝለፍልፎ ተኝቷል። አንዳንዱ ለብቻው ነው። የተወሰነው ከአጠገቡ ሰው ነበር። ከማስታውሰው አንድ በሰላሳዎቹ እድሜ ክልል የሚገኝ ሰው ሲያጣጥር ነበር። እህቱ ትሁን ጓደኛው ሰዎች አንስተው እርዳታ ወደ ሚሰጥበት ቦታ እንዲወስዱላት ተማፀናለች። እዚያ አከባቢ ከነበረው ሰው እንደዚያ አይነት አቅምና ሞራል ያለው ሰው አልነበረም። መጨረሻውን አላየሁም ተነስቼ ሄድኩ። ስለ ወንድሞቼ ሳስብ በነበረበት ሰዓት መንገድ ላይ አንዱን ወንድሜን አግኝቼው ከአንዱ ወንድማችን ስልክ በስተቀር የሶስቱን እንዳገኘና ብዙ እሬሳ ወደ ቡሾፍቱ ሆስፒታል እየተወሰደ ስለሆነ እዚያ ሄደን እንይ አለኝ። ሆስፒታሉ ውስጥ የተደረደረውን እሬሳ ሳይ አጥወለወለኝ። ወንድሜን እንዲያይ ነግሬው እኔ ፈጥኜ ወጣሁ። ወንድሜ እንደነገረኝ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ብቻ ከሰማኒያ በላይ እሬሳ መጥቶ እንደተደርደረና ብዙዎቹ በጭቃ የተለወሱ መሆኑን ጥቂት የማይበሉ በጥይት የተመቱ መሆኑንና በጥይት የተመቱትን ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ ለብቻ እየለዩ መሆኑን ነገረኝ። ወንድማችን እዚያ ውስጥ የለም። በዓይን የምናውቀውንም እያየ ስለነበር የሚያውቀው ሰው እንደሌለ ነግሮኝ ተያይዘን ወጣን። በዚህን አጭር ጊዜ ይህን ያህል እሬሳ ተስብስቦ ከመጣ በየጥጋጥጉ፤ በገደሉና ውሃ ውስጥ ያሉ የሞቱ ሰዎች ብዛት ሳስብ ዘገነነኝ። በዚያ ላይ በየ መንገዱ ሲያጣጥሩ የነበሩና የህክምና እርዳታ ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች እጣቸው ምን መሆን እንደሚችል ካሰብን ከአእምሮ በላይ ይሆንብናል። ይህንን ይተቀነባበረ ይህወሃት ሴራ በአጋጣሚ የተፈጠረ ነው ብለን ካሰብን ሞኞች ነን። ይህ ሆን ተብሎ በአንድ ላይ የገኙትን የኦሮሞ ምሁራንና ቄሮዎችን ለመጨፍጨፍ የታቀደ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም።
ከጓደኛዬ ጋር ብንጠፋፋ ብለን ጧት የተቀጣጠርንበት ቦታ ሄድኩና ምንም ሳይሆን ጧት እንደነበረ አገኘሁት። የእድል ጉዳይ ገረመኝ። ብዙዎቹ ከአጠገባችን እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል። ገሚሶቻችን የሞት አፋፍ ላይ ደርሰን ተመልሰናል። እንደ ጓደኛዬ ያሉት ደግሞ ምንም ነገር ሳይደርስባቸው አምልጠዋል። እኔም ዋቃ አትርፎኝልና በወንድሞቼና እህቶቼ እልቂት ከመብሰልሰል ውጪ ስለ ራሴ ምንም ቅሬታ የለኝም። የወገኔ ደም በከንቱ ፈሶ እንደማይቀር ደግሞ እርግጠኛ ነኝ። በአምቦ፤ በመቂ፤ በባቱ/ዝዋይ፤ በቡሌ ሆራ፤ በሻሸመኔ፥ በኮፈሌ፤ በአወዳይና ሀረር፤ በምእራብና ምስራቅ ወለጋና ሌሎችም ቦታዎች እንደ ታየው የወገን ደም ፈሶ እንደማይቀር ማሳየትና ይህንን እረመኔ ቡድን ማስወገድ ነገ ሳይሆን ዛሬ፤ ዛሬ ሳይሆን አሁን መሆን አለበት።

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: