በኢትዮጵያ ህዝብ የሚደረገው የእምቢተኝትና የአመጽ ትግሎችና በህወአት አገዛዝ ስር የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት

ነዓምን ዘለቀ

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየተደረገ ያለው የእምቢተኘነትና የአመጽ ትግል ሳይቋረጥ ከመንፈቅ በላይ ባስቆጠረበት በአሁኑ ወቅት፣ ህወሃት እተማመንበታለሁ የሚለው የመከላከያ ሰራዊት ኣባላት፣ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚከተለው የዘረኝነት፥ የኣድሎና የበደል ፖሊሲ ትክክል አለመሆኑን ተገንዝበው ህዝባዊ ትግሉን በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ። በዕለተ ዕሁድ ነሃሴ 29 ፥ 2008 ከ450 በላይ የሚሆኑ ወታደሮች በሰሜን ጎንደር የሚደረገውን ህዝባዊ ተቃውሞውን በመደገፍ ወያኔን በማስወገዱ ሂደት ተጋድሎ እንደሚያደርጉ ማሳወቃቸው፣ የወያኔ ስርዓት እያከተመለት መሆኑን አመላካች ነው። ከዚህ በፊትም፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የጀግንነት ስራ ሰርተዋል። የህዝባዊ እምቢተኝነቱን ትግል ሲቀላቀሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በምርጫ 97 ወገን ላይ ተኩሱ ሲባሉ አሻፈረኝ በማለት ሄሊኮፕተር ይዘው ወደጎረቤት አገራት አምልጠዋል።

መከላከያ ሰራዊት ኣባላት የህዝቡን ስቃይ ሰምቷዋል፣ አሁን ደግሞ የህዝቡን ድምፅ አስተጋብቷል፣ እንደወገኑ ሁሉ የወያኔ አገዛዝ “በቃኝ” አያለ ይገኛል። የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ለወራት የታገለውን፣ የአማራ ክልል ህዝብ የሞተለትን አላማ አንግቦ በመነሳት ላይ ይገኛል ። ህዝብና ሰራዊት የአንድ አገር ክፋዮች፣ የአንድ አገር ገጽታዎች ናቸው። ከ90% በላይ የሆነዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንደ ሲቪል ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ሁሉ ከአንድ ብሄር የበላይነት ተላቅቆ ሰላም፥ ፍትህና እኩልነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ ዉስጥ መኖር ይፈልጋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጽኑ ፍላጎት ምንም አይነት ጭቆናና መድሎ በሌለበት ስርዓት ዉስጥ ከአባቶቹ የተረከባትን አገር የግዛት አንድነት አስከብሮ ለሚቀጥለዉ ትውልድ ማስረከብ ነዉ እንጂ ወያኔና ምዕራብያውያን እንደሚያስቡት ለ “ምግብ ለመኖር” ብቻ የሚዋጋ ሰራዊት አይደለም።

“ውትድርና ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን አምባገነን ነው።” ሆኖም ትክክለኛ ውለታውን የሚያከብርለት ጠንካራ አመራር ይፈልጋል። የታችኛው ሰራዊት የበላይ አመራሩን ጀግና፣ ትክክለኛና በውትድርና ሳይንስና ዕውቀት የታነጸ ክህሎት ያለው አድርገው ለማመን ለመከተልም ይፈልጋሉ።

ወታደሩ በዘር በተመሰረተ አድሎ ሳይሆን፣ በተግባር፥ በልምድና በአገልግሎት ላይ የተመሰረተ ዕድገት፣ የደሞዝ ጭማሪና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እንዲሰጠው ይፈልጋል።

ሰራዊቱ አገራዊ ግዳጁን በሚወጣበትና በአገልግሎት ላይ ባለበት ግዜ ሁሉ ለስራዉ የሚያስፈለገዉን ቁሳቁስ ሁሉ መንግስት የማቅረብ ግዴታ አለበት፥ ይህ ሎጂስቲክን፥ ወታደራዊ ዩኒፎርሙንና የምግብ አገልግሎትን ያጠቃልላል።

ሞራሉ የላሸቀና አቅምና ብቃት በሌላቸው የህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ ጄኔራሎች የሚመራ ሰራዊት፣ ሙሰኛና ኢፍትሃዊ የሆነን ስርዓት ማገልገል አለመፈለጉ ብቻ ሳይሆን አገሩን ከጠላት መከላከልም አይችልም። የህዝብ ትግል ሲጎመራ፣ ሰራዊቱ በዘራፊና ዘረኛ ኣዛዦቹ ላይ አመጽ ማቀጣጠልና አፈሙዙን ወደ አነዚህ ጨቋኞች መመለሱ አይቀሬ ይሆናል።

ህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነዉ።ኣምባገነናዊ ጸረ-ሕዝብ ስርዓት ነው። ኢትዮጵያን የሚመራዉም በኣንድ ብሔር የበላይነት ላይ በተመሰረ ኣስተሳስብና ከዚሁ በሚመነጩ ፖሊሲዎች ነዉ። የወያኔ ስርዐት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠይቀዉን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የማይችል ስርዓት ነዉ። ህወሓት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠይቀዉን ጥያቄ መመለስ የማይፈልገዉ የጥያቄዎቹ መልስ የሱ መጨረሻ መሆኑን ስለሚያዉቅ ነዉ።

አሁን ያለው የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራር ኢትዮጵያ ዉስጥ መሳሪያ አንስተዉ በተለያዩ ግንባሮች የሚንቀሳቀሱ አማጽያንን ለማጥፋት የሚያስችለዉ ምንም አይነት ህዝባዊ ድጋፍ የለውም። በመጠነ-ሰፊ ችግሮችና ቅራኔዎች የተዘፈቀ ሰራዊት በሁሉም ኣቅጣጫ በሚጠመድ የህዝብ ትግል ኣካል ይሆናል አንጂ በህዝብ ላይ የማያባራ መከራና ግፍ ለሚፈጽም የዘረኛና የጨቋኙ የህወሃት አገዛዝ መሳሪያ ሆኖ በረጅሙ ሊቀጥል ኣይችልም።

በህወሃት አገዛዝ ስር የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ሞራል እጅግ የላሸቀ ነው። መንፈሱ የደከመ፣ አንድነቱ የላላ፣ በራሱ የማይተማመን እርስ በእስር በጎሪጥ ኣንዲተያይ የተደረገ፡ ዘረኛና ዘራፊ ጄኔራሎች የሚያዙት ነው። እንዲህ አይነቱ ሰራዊት ደግሞ በአንድነት በረጅሙ ለመዋጋት የሚያስችለው ሆኔታ ውስጥ የሚገኝ ኣይደለም።

ናፖሊዮን “መንፈሰ ጠንካራ ሰራዊት የራሱን ሶስት እጥፍ ወታደር ያሸንፋል’” በማለት አንድ ሰራዊት ሊኖረዉ ስለሚገባ የመንፈስ ጥንካሬና ሞራል ወሳኝነትና አስፈላጊነት ተናግሯል። ይህን ያለዉና ታላቅ የወታደራዊ ስትራቴጂና ታክቲክ ክህሎት አንደነበረው በሰፊው የተጻፈለት ናፖሊዮን፣ 300,000 አባላት የለዉን “ታላቁ ሰራዊት” ይዞ የተሸነፈዉ የሽምቅ ውግያ በገጠሙት ስፓኒሾችን በስፓንያ በሰራዊቱ ላይ ያደረሱበት ቡርቦራ አይነተኛ ምክንያትና ለውድቀቱም ከትልልቆቹ መንስኤዎች ኣንዱ ነበር። ከናፖሊዮን በኋላ ሽምቅ ተዋጊዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ አገሮች ዉስጥ ትልልቅ መደበኛ ሰራዊቶችን ለሽንፈት ተደርገዋል። አልጄሪያ፥ ቻይና፥ ቬትናምና በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት የነበረችዉ አፍጋኒስታን የሽምቅ ዉግያ አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸዉ። በሽምቅ ውጊያ የደርግን ስርዓት በማዳከም መቻላቸውም ከምክንያቶች አንዱ ሆኖ ስልጣን ላይ የወጡት የህወሃት መሪዎች ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በአራቱም ማዕዘን የገጠማቸዉን የአማጽያን እንቅስቃሴ ማሸነፍ የሚችሉበት ምንም አይነት ህዝባዊ ድጋፍ ሰለሌላቸዉ እነሱ በመጡበት መሸነፋቸዉ አይቀርም። ህወሃት ሽምቅ ተዋጊዎች ለማጥፋት የሚያደርገው “ቆሻሻ ጦርነት” ከጦር ወንጀለኝነት ጋር ስለሚያያዝ፣ በአለም አቀፍ ማህበረሰብም ይሁን በኢትዮጵያውያን መመርመሩ አይቀርም። ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ህወሃት የሚደረግለት ድጋፍ መቀነሱ አይቀርም። አሁን እንደሚታየው በህወሃትን ስር የሚማቅቀው ሰራዊት ጠንካራ የተቀናበረ ሽምቅ ውጊያና የህዝብ ኣልገዛም ባይነት በሁሉም የኢትዮጵያ ኣካባቢዎች ከተጠመደና ከተቀጣጠለ ኣገዛዙም “የስፓኝ ነቀርሳ” ይሆንበትና ወደ መፍረክረኩ ለጥቆም ኣብዛኛው የሰራዊቱ ኣባላት ወደ ህዝብ ትግል የሚቀላቀሉበት ሂደት ይፈጠራል።

ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚገኙ ስር የሰደዱና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጠያቂዎቹ የሆኑት የህወሓት መሪዎችና የትግራይ ጄኔራሎች ናቸዉ። የእነዚህ መሪዎችና ጄኔራሎች ዘረኝነት፥ ጭካኔ፥ ስግብግብነትና ገንዘብ ማሸሽ አገራቸዉን ዋጋ እንደሚያስከፍል ሁሉ እነሱንም ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ሊያዉቁ ይገባል። የኣምባገነናዊነትና የዘረኝነት ተግባሮች የሌላ ብሄር ዜጎችን እንደሁለተኛ ዜጋ፡ ከዚያም በታች የመቁጠር አባዜያቸው፥ ለከት ያጣው ኢፍትሃዊ ተግባሮቻቸው፥ ዘረፋቸው፡ ኣፈናና ጭቆናቸው ሳቢያ ከህዝቡም ሆነ ከኣብዛኛው የመከላከያ ሰራዊት ኣባላት የተነጠሉ መሆናቸውን ሊያውቁ ይገባል። ይህንን ሁሉ በአይኑ የሚያየዉና የገፈትና የመከራ ህይወት ኣስከኣፍንጫው የተጋተው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ትዕግስቱ ተሟጥቶ አልቋል። በኦሮሞ ክልል ኣየታየ የሚገኘው ህዝባዊ የቁጣ ማዕበል ፡ ዛሬ በጎንደርና በጞጃም ዉስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመደገም ላይ የሚገኘው በማያሻማ ሁኔታ ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው። ትግሉ በመላ የኢትዮጵያ ኣካባቢዎች የሚዛመትበትና የሚቀጣጠልበት፡ የወያኔ ኣርነት ትግራይ ኣገዛዝ እውር ድንብሩ ወጥቶ የሚጨብጠውን የሚለቀውን የሚያጣበት፥ ብሎም ተፍረክሮኮና ተንኮታክቶ በህዝብ ትግል የሚንበረክክበት ጊዜ እሩቅ ኣይሆንም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነት ለፍትሃና ለአኩልነት የሚያደርገው የአመጽ ትግልና የኣልገዛም ባይነት ትግል፥ የህዝባዊ አምቢተኝነት ትግሎች ሁሉ የህወሓት ኣገዛዝ እስኪወገድ ድረስ በየኣካባቢው አንደ ሰደድ አሳት የሚቀጣጠል እንጂ የሚቆም ኣይሆንም።

(ቀደም ሲል ለንባብ ከወጣው ሰፊ መጣጥፍ የተወሰደ)

Bilderesultat for ethiopian soldiers

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: