ተመድ ለመላክ ያሰበውን የሰብዓዊ መብት አጣሪ ቡድን መንግሥት እንደማይቀበል አስታወቀ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ካውንስል በኢትዮጵያ ሰሞኑን በተካሄዱት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማጣራት የጠየቀውን ፈቃድ መንግሥት ውድቅ አደረገ፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች በተነሱት ተቃውሞዎች የሟቾችና የተጐጂዎች ቁጥጥርን አስመልክቶ በመንግሥት እየወጣ ያለው ሪፖርት ተዓማኒነትን በመጠራጠር ነው፣ የተመድ ሰብዓዊ መብት ካውንስል ጥያቄውን ያቀረበው፡፡

በሰብዓዊ መብት የተመድ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ዚያድ ራድ አል ሁሴን ለተለያዩ የውጭ የሚዲያ ተቋማት እንደተናገሩት፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. የተደረጉትን ተቃውሞዎች አያያዝ ለማጣራት ተዓማኒነት ያለው ሙከራም ሆነ ተጠያቂነት በመንግሥት በኩል አለማየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተቃውሞው ወቅት የተገደሉ ዜጐችን ቁጥር በትክክል ለማወቅ አለመቻሉንም ገልጸዋል፡፡ በማከልም መንግሥት ሰላማዊ ተቃውሞ በማድረግ ላይ ሳሉ ያሰራቸውን ዜጐች በፍጥነት መልቀቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያና በአማራ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ተቃውሞዎችን አስመልክቶ ባደረገው ማጣራት፣ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ተመጣጣኝ ኃይል መጠቀሙን በአማራ ክልል ግን ተመጣጣኝ ኃይል አለመጠቀሙንና ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ማለቱ ይታወሳል፡፡ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ሂውማን ራይትስ ዎች ግን በኦሮሚያ ክልል ብቻ 400 ሰዎች መገደላቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከቀረበው 178 ሰዎች ሞት ሪፖርት በእጅጉ ይርቃል፡፡

የተመድ የሰብዓዊ መብት ካውንስል ቃል አቀባይ የሆኑት ራቪያን ቫ ማዳስኒ፣ ‹‹እየቀረቡ ያሉት ሪፖርቶች በእጅጉ ይለያያሉ፡፡ በተለይ በመንግሥት የቀረበው የሟቾች ቁጥር ትንሽ በመሆኑ ተመድ በራሱ ቡድን ማጣራት ይፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ተመድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደማይልክ የገለጹት ቃል አቀባይዋ ሆስፒታሎችን የሚጐበኙ፣ የዓይን እማኞችንና የፀጥታ ኃይሎችን የሚያነጋግር ቡድን ብቻ ለመላክ ጥያቄ ማቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹ተመድ የፈለገውን አስተያየት ሊይዝ ይችላል፡፡ የዜጐችን ሰብዓዊ መብት የመጠበቅ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነት ነው፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ለአልጄዚራ ገልጸዋል፡፡

‹‹የተመድ አጣሪ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አያስፈልገውም፡፡ ምክንያቱም ተመድ በኢትዮጵያ የተለያዩ ተቋማት አሉት፤›› ሲሉ አቶ ጌታቸው አስታውቀው፣ የፀጥታ አስከባሪዎች ያላግባብ ኃይል ተጠቅመው ከሆነም መንግሥት በራሱ እንደሚያጣራው ተናግረዋል፡፡

የተመድ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ቡድኖችን በመከልከል በተደጋጋሚ ስሟ የሚጠራው ኤርትራ መሆኗ ይታወቃል፡፡

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: