የሰራተኛው ኑሮ በደርግና በወያኔ ዘመን (በገለታው ዘለቀ)

ከ25 ዓመታት በፊት አንድ የኮሌጅ ዲፕሎማ የነበረው ኣስተማሪ ሲቀጠር የመነሻ ደመወዙ 347 ብር ነበር። ይህን ገቢ በወቅቱ ከነበረው የዶላር ምንዛሬ ኣንጻር ስናየው 173.5 ዶላር ይመዝን ነበር። ይህ ኣስተማሪ ገና ሲቀጠር የቀን ገቢው 5.8 ዶላር ነበር ማለት ነው። ከፍ ያለ ነበር። ከ25 ኣመት “እድገት” በሁዋላ በህወሃት ኢህዓዴግ ዘመን ኣንድ የኮሌጅ ኣስተማሪ ዲፕሎማውን ይዞ ሲቀጠር 1663 ብር ቢከፈለው ኣሁን ባለው ምንዛሬ ሲታይ 77.3 ዶላር ያገኛል። ይህ ማለት የቀን ገቢው በዶላር 2.57 ሳንቲም ነው ማለት ነው። ይህ ማለት የደርግ ጊዜው ኣስተማሪ ደመወዝ ከህወሃት ኢህዓዴግ ጊዜ ኣስተማሪው ደመወዝ ከሁለት እጥፍ በላይ ይበልጣል ማለት ነው። በዓለም ኣቀፍ ደረጃ የድህነት ወለል የሚባለው ሁለት ዶላር ኣካባቢ ሲሆን ይህ በህወሃት ኢሃዴግ ዘመን የኮሌጅ ዲፕሎማ የያዘው ኣስተማሪ በዚያው በድህነት ወለል ኣካባቢ ነው ማለት ነው። ነገር ግን በደርጉ ጊዜ ከሃያ ዓምስት ዓመት በፊት የነበረው ዲፕሎማ ኣስተማሪ በቀን የሚያገኘው ገቢ ወደ 6 ዶላር የሚጠጋ ሲሆን እጅግ በተሻለ ህይወት ውስጥ የነበረ በዓለም ኣቀፍ የገቢ መለኪያም የተሻለ ገቢ የነበረው ነበረ። በኣሁኑ ሰዓት ኣንድ የሁለተኛ ደረጃ ኣስተማሪ ሲቀጠር 2197 ብር የሚያገኝ ሲሆን ይህ ማለት 102 ዶላር ማለት ነው። ይህ መምህር በቀን 3.40 ሳንቲም የሚያገኝ ሲሆን በደርግ ጊዜ ዲፕሎማው ወደ 6 ዶላር የሚጠጋ በቀን ያገኝ ስለነበር በደርጉ ጊዜ የነበረ ያ ጀማሪ የዲፕሎማ መምህር የዛሬውን የዲግሪውን መምህር ክፍያ በጅጉ ይበልጠዋል። በዚህ ቀላል መንገድም ሆነ በፈለገው የኢኮኖሚክ ሞዴል ብናሰላው በህወሃት ኢህኣዴግ ጊዜ ያለው ሲቪል ሰራተኛ ገቢ ከደርጉ ጊዜ መምህር በጅጉ ወርዶ እናያለን። በደርግ ጊዜ ኣንድ የሁለተኛ ደረጃ ኣስተማሪ ሲቀጠር የቀን ገቢው ወደ ዘጠኝ ዶላር የሚጠጋ ሲሆን በኣሁኑ ጊዜ የሚቀጠረው መምህር 3.40 ሳንቲም ብቻ በመሆኑ ልዮነቱን ማየት ይቻላል። የነዚህን የሁለት ዘመናት መምህራን ለማወዳደር ኣንዱ ሌላው ነገር ደግሞ የግሽበትን (inflation) ጉዳይ ኣንስተን ነው። በደርግ ጊዜ ያ 347 ብር ያገኝ የነበረ መምህር ኣንድ ዳቦ በኣስር ሳንቲም ይገዛ ነበር፣ ኣንድ እንቁላል በኣስር ሳንቲም ይገዛ ነበር። ኣሁን 1663 ብር የሚያገኘው ደግሞ ኣንድ ዳቦ በኣማካይ ኣንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ቢገዛ ኣንድ እንቁላል ሶስት ብር ይገዛል። በሃያ ኣምስት ዓመታት እንቁላል የ3000% ጭማሪ ሲያሳይ ዳቦ በ1500% ጨምሯል። የመምህሩ ገቢ ደግሞ የዋጋውን ግሽበት የሚፎካከር ሆኖ ኣያድግም። ደመወዝ ደግሞ አራት መቶ ፐርሰንት ገደማ ብቻ ነው ያደገው። ለናሙና በጠቀስናቸው እንቁላልና ዳቦ የዋጋ ጭማሪ ጋር የደመወዙ ጭማሪ ሲወዳደር ከፍተኛ ክፍተት (gap) የሚያሳይ ሲሆን ይህ ክፍተት ነው የመምህሩን ትዳር የማሸነፍ ኣቅም መድከም የሚያሳየው። ዳቦና ደመወዝ ሲወዳደሩ ዳቦ በኣንድ ሺህ ፐርሰንት ቀድሟል። እንቁላልና ደመወዝ ሲወዳደሩ እንቁላል ከሁለት ሺህ ኣምስት መቶ ፐርሰንት በላይ ቀድሞ ሄዷል። እናም የዛሬው መምህር ቁርሱን እንቁላል በዳቦ ለመብላት ይሄን ያህል ደክሟል ማለት ሲሆን በኣንጻሩ የደርጉ ጊዜ መምህር በየቀኑ ያለ ኣሳብ መመገብ ይችላል። የደርጉ ጊዜ መምህራን በተለይ በገጠሩ ኣካባቢ ህብረተሰቡ ቤት ይሰጣቸው ስለነበር የቤት ኪራይ ኣያስቡም። ከተማም ቢሆን የቤት ኪራይ ኑሯቸውን የሚፈታተን ባለመሆኑ ከቁም ነገር ኣይቆጥሩትም ነበር። የህወሃት ኢሃዴግ ጊዜ ኣስተማሪ በተለይ በከተሞች ኣካባቢ የሚኖረው ኑሮ ምን ያህል እንደሚከብደው መገመት ኣያዳግትም። በደርጉ ጊዜ የነበሩ መምህራን ደመወዛቸው ከኑሮው ጋር ከዓለም ኣቀፍ የድህነት ወለል ኣንጻር ከፍ ያሉ ስለነበሩ ለቤተሰብ ኣምሳም፣ መቶም ብር ከዚያም በላይ ተቆራጭ ኣድርገው ይጦሩ ነበር። የህወሃት ኢሃዴግ ጊዜ ኣስተማሪ ለቤተሰቡ ተቆራጭ ኣድርጎ መርዳቱ ቀርቶ እሱ ራሱን ችሎ መኖር ከብዶት ይታያል። አሁን የመምህሩን ኑሮ ከደርግና ከኣሁኑ ጋር እያወዳደርኩ የምገልጸው ለናሙና እንጂ ኣጠቃላይ የሲቪል ሰራተኛው ኑሮ በዚህ ችግር የሚገለጽ ነው። የኢትዮጵያ ሲቪል ሰራተኛ ባለፉት ሃያ ኣምስት ኣመታት በዚህ መንግስት በጣም የተጎዳና ሲታለል የኖረ ነው።ያሳዝናል። ኑሮ እንዲህ ቁልቁል ሲሆን ገቢ እንዲህ ቁልቁል ሲሆን… እውነተኛ ፓርላማ ቢኖር ይህ ጉዳይ ከባድ ኣገራዊ ጉዳይ ሆኖ ክርክር ሊደረግበት መፍትሄ ሊሰጠው ይገባ ነበር።
.
እዚህ ጋር ኣንድ የሚነሳ ነገር ይኖራል። የመምህሩ ደመወዝ ከደርግ ጊዜው ጋር ሲነጻጸር በአሃዝ ጨምሯል ። ነገር ግን በዶላር ሲሰላ ደግሞ እየቀነሰ መጥቷል፣ ከግሽበቱ ጋር ሲሰላ ደግሞ ከዛሬ ሃያ አምስት ኣመት ከነበረው ጋር ሲታይ ኣስደንጋጭ ለውጥ ኣለ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ልንል እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጀ የኢትዮጵያ መንግስት ደመወዝ የሚጨምርበትን ስልት ማወቅ ኣለብን። የኢትዮጵያ መንግስት ደመወዝ የሚጨምረው ኣገሪቱ ስላደገች ኣይደለም። ጭማሪው ሃገሪቱ የተሻለ ኣምርታ ያ ምርት ወደታች መንቆርቆር ስለጀመረ ኣይደለም። ጭማሪው የምርት (GDP) መጨመር ያመጣው ሳይሆን መንግስት የሆነ ዘመን ላይ የህዝቡን የተቃውሞ ስሜት ያይና ይህንን ተቃውሞ የሚያበርድበትን መንገድ ያስባል። እናም ለደመወዝ ጭማሪው ሲል ብቻ ገንዘብ በገፍ ያትማል። በመሰረቱ የኣንድ ሃገር የገንዘብ ህትመት መጠን የሚወሰነው በሃገሪቱ ኣጠቃላይ ምርት (GDP) መጠን ነው። ገንዝብ ማለትም የኣንድን ሃገር ጠቅላላ ምርት ወይም GDPን የምናካፍልበት መሳሪያ ነው እንጂ በራሱ ወረቀት ነው። መንግስት ለዚህ ብዙ ግድ የለውም። ታዲያ መንግስት ገንዘብ በገፍ ያትምና ለጊዜው ለሰራተኛው ከፍ ያለ ቁጥር በማሳየት የሲቪሉን ሰራተኛ ኣፍ ለመያዝ ይሞክራል። ነገር ግን የቁጥሩ ጭማሪ እድገትና ብዙ ምርት ገፍቶት የመጣ ባለመሆኑ መንግስት ደመወዝ በጨመረ በማግስቱ ሁሉ ነገር ይጨምራል። ኑሮ ውድነቱ ሰማይ ይደርሳል። ለምን ይሄ ሆነ ስንል ከፍ ሲል እንዳልነው ጭማሪው በህትመት ላይ ያተኮረ እንጂ የሃገር እድገት ውጤት ባለመሆኑ ነው። የተመረተው ምርት በሃገሪቱ ከታተመው ገንዘብ ጋር ስለማይመጣጠን ብሮች ይጋሽባሉ። ዋጋ ያጣሉ ማለት ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ የሲቪል ሰራተኛውን ደመወዝ ጉዳይ ስናይ የሰራተኛው ሪል ገቢ አየቀነሰ ይሄዳል እንጂ እየጨመረ ኣይሄድም። የጨመረው ከላይ የምናየው ቁጥሩ ሲሆን ከግሽበት ኣንጻር ሲሰላ ግን ከደርጉ ጊዜ መምህር የኣሁኑ መምህር ገቢ በጣም ቀንሷል። እንዲህ እየሆነ ነው ላለፉት ሃያ ኣምስት ኣመታት የኖረው። ህወሃት ኢሃዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ደመወዝ ይጨመራል ነገር ግን ደመወዝ በተጨመረ ቁጥር የሰራተኛው ኑሮም ከኣምናው ዘንድሮ እያቃተው የመጣበት ምስጢር መንግስት ቁጥር እያሳየ ኣንደኛ ገቢው በዶላር ሲሰላ እየወረደ ይሄዳል ሁለተኛውና ዋናው ጉዳይ ደግሞ ጭማሪው እድገት የገፋው ባለመሆኑ ከግሽበቱ ጋር ተፎካክሮ ሊቆም ኣልቻለም። አንዱ የምርት ውጤት ከህዝብ ብዛት ጋር ሳይጣጣም ቀርቶ የመጣው ችግር ሲሆን ሌላው ችግር ደግሞ ያለችውን ሃብት ወደ ኣንድ ኣቅጣጫ የማዛወር ስራ እየተሰራ ስለሆነ ነው። መንግስት ያለችውን ምርት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊያከፋፍል ቢችል ኣገሪቱ ይህን ያህል የሚያመረቃ እድገት ስላላሳየች ኣጥጋቢ ደመወዝ ባይገኝም ከደርግ ጊዜ ግን ሊቀንስ ኣይገባውም ነበር። ኢትዮጵያ በእርዳታ መቀበል ከሰሃራ በታች ካሉ ኣገራት ቀዳሚ ናት። በኣሁኑ ሰዓትም የመንግስትን ባጀት ከ 50-60% የሚደርሰውን የሚሸፍነው ከተባበረችው ኣሜሪካ፣ ከኣወሮፓ ህብረትና ከሌሎች ለጋሾች በሚገኝ ርዳታ ነው። ኢትዮጵያ በዓጼ ምኒሊክ ዘመን ራሷን የቻለች ኣገር የነበረች ሲሆን በኣጼ ሃይለስላሴ ዘመንም የተሻለች የተከበረች ኣገር ነበረች። በደርግ ጊዜ በእርዳታ ላይ መደገፋችን ከፍ ብሎ የታየበት ዘመን ሲሆን ከእርዳታ የሚገኘው የመንግስት ባጀት ሽፋን ግን ዝቅተኛ ነበር። ደርግ በህይወት ዘመኑ ያገኘውን ርዳታ የኣሁኑ መንግስት በኣንድ ኣመት ጊዜ ኣግኝቶታል። በዚህ መንግስት ግን ከፍ ሲል እንደገለጽነው ከግማሽ ኣካላችን በላይ በርዳታ ላይ የተደገፍን ሲሆን ይህ ርዳታ ቢያቆም የሃገሪቱ መንግስት ሊፈታ ይችላል።
.
ወደ ስራተኛው ደመወዝ እንመለስና ያለችውን ሃብትና እርዳታ በተገቢው መንገድ ስለማንካፈል ከደርጉ ጊዜ ሰራተኞች ኑሮ ያሁኑ ከእጥፍ በላይ ወድቋል:: ለዚህም ሌላው ምክንያት ደግሞ ለሰራተኛው የተወሰነ ቁጥር እያሳዩ በዘዴ የሃብት ዘረፋ እየተደረገ ስለሆነ ነው። ሲቪል ሰራተኛው በየዓመቱ እየደከመ የሚሄድበት ምስጢርም ከሰራተኛው ጉልበት ላይ እየቀነሱ የነ ኤፈርትን ሃብት እያደለቡ ስለሆነ ነው። ሲስተማቲክ የሃብት ዝውውር ይባላል ይህ ኣይነቱ ዘዴ። የህወሃት ካምፓኒዎች በጣም እያደጉ ሃብት እየጨመሩ ሲሄዱ ሰራተኛው ትንሽ የቁጥር ጨዋታ እያየ ነገር ግን ከኣምናው ዘንድሮ ትዳር የማሸነፍ ኣቅሙ እየወረደ ያለው በዘዴ የጉልበት ዋጋ ዝውውር እየተደረገ ስለሆነ ነውና ሲቪል ሰራተኛው ለመብቱ ሊታገል ይገባዋል።
ዋናው ነገር መንግስት ኣስር ጊዜ በኢኮኖሚ አደግን እያለ የሚለው ነግረን ነገር ተጽእኖው በሲቪሉ ሰራተኛ ላይ ኣይታይም። ኣይታይም ብቻ ሳይሆን ሰራተኛው በዘዴ እየተዘረፈ ድህነት እየጨመረ ነው የመጣው።ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ጉዳይ በተመለከተ በሌላው ዓለም ባልተለመደ ሁኔታ በሁለት ጎራዎች ከፍተኛ ክርክር ይታያል። ክርክሩ ኢትዮጵያ በያዘችው የእድገት ኣቅጣጫ ሳይንስ ላይ ሳይሆን እድገት በኢትዮጵያ አለ የለም በሚል ነው። ለዚህ ነው በሌላው ዓለም የተለመደ ክርክር ኣይደለም የሚያስብለን። መንግስትና ደጋፊዎቹ ሽንጣቸውን ገትረው ባለፉት ሃያ ኣመታት በተለይም ባለፉት ኣስር ኣመትታ ከፍተኛ እድገት ኣሳይተናል፣ እድገቱ ደግሞ በፍጥነቱ ከዓለም ከፍተኛ ደረጃ ይዟል፣ ከኣፍሪካ ኣንደኛ ነን እነ ጋና፣ ሞሪሺየስ፣ ኣንጎላ ሁሉ እኛ ያሳየነውን ፈጣን እድገት ኣላሳዩም የሚል ነው። በጥንድ ቁጥር ነው ያደግነው የሚል ነው። ይህን የሚቃወመው ሰፋ ያለው ማህበረሰብ ደግሞ ኣንዳንዴ ያፌዝበታል ኣንዳንዱ ደግሞ ከመንግስት ሰዎች ጋር ሸንጡን ገትሮ ይከራከራል። ክርክሩን ኣስደማሚ የሚያደርገው በራሱ እድገት ኣለ የለም የሚለው ነገር መከራከሪያ መሆኑ ነው። ልክ እድገት የማይጨበጥ የማይዳሰስ ይመስል ክርክሩ መነሳቱ ኣስደማሚ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ትንሽ ምክንያታዊ መሆን የፈለጉ ወገኖች እድገትና ልማት የሚሉትን ጽንሰ ሃሳቦች ይከፋፍሉናል በኢትዮጵያ ውስጥ እድገት ኣለ ነገር ግን ልማት የለም የሚል ነው። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እድገት የሚለውን ኣሳብ የሚገልጹት ጠበብ ኣድርገው ነው። እድገት ማለት የGDP ጭመራ ማለት ነው በአጭሩ። በየዓመቱ GDP ከጨመረ የኢኮኖሚ እድገት ታየ ለማለት ያስችላቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የኢኮኖሚ ልማት ሲሉ በአብዛኛው ተቀባይነት ያለው ኣሳብ ልማት ማለት ልክ እንደ ኢኮኖሚ እድገት በቀላሉ የሚለካም ኣይደለም። ሰፋ ያለ ጽንሰ ሃሳብ ሲሆን ዋናው ጉዳይ ግን ያ ኣለ የተባለው የኢኮኖሚ እድገት ያመጣቸውን ተጽእኖዎች የሚመለከት ነው። ተጽእኖው ከሚገለጽባቸውን ጉልህ ጉዳዮች ደግሞ በኣብዛኛው HDI (Human Development IndeX) በመባል የሚታወቀውን መለኪያ ያካትታል። ይህ ማለት በኣንድ ፖለቲካ ጠገግ ውስጥ ያሉ ዜጎች በሶስት ዋና ዋና ኣቅጣጫ (Dimension) ለውጥ ሲያሳዩ ማለት ነው። እነዚህ ጉዳዮች ኣንደኛ ረጅም እድሜ (long and healthy life) ሁለተኛ የእውቀት የትምህርት ልማት ሶስተኛ የኑሮ ደረጃ ( A decent standard of living ) ናቸው። የኢኮኖሚ እድገት ሲባል እንግዲህ የሃገሪቱ እድገት በነዚህ ኣቅጣጫዎች የዜጎችን ህይወት ሲቀይር ነው ማለት ነው። ዞሮ ዞሮ የኢኮኖሚ እድገት ወይም የ GDP ጭምራ ኣላማ በዚህ ዓለም ላይ ለሰው ልጆች እድገትን ለማምጣት በመሆኑ ብዙ ጊዜ ስለ ሃገር እድገት ሲነሳ የ GDP ጭመራው ብቻ ሳይሆን HDI መሻሻልን ይመለከታል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድግጅቶችና ኣብዛኛው ድሃ የሚባለው ህዝብ ብዙ ጊዜ እድገትን ከHDI ጋር እንዲያያዝለት ይፈልጋል። ስለሆነም በኣንድ ኣገር ውስጥ ኣንድ መንግስት የኢኮኖሚ እድገት ማምጣቱን እንደ ድል ኣድርጎ ቢጨፍር ኣብዛኛውን ህዝብ ኣያስደምመውም። ኣብዛኛው ህዝብ የሚደሰተው ያ እድገት በ HDI ላይ ተጽእኖው ሲያርፍ ነው።
.
ወደ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ እንመለስና መንግስት ከፍተኛ እድገት ኣስመዝግቢያለሁ ይላል። ነገር ግን ከፍ ሲል እንዳየነው እድገቱ በሲቪል ሰራተኛው ላይ ኣይታይም። ሰራተኛው ባለበት እንኳን ሳይቆም ከግሽበቱ ኣንጻር ገቢው ከደርግ ጊዜው መምህር በጣም ቀንሷል:: ይሁን እንጂ መንግስት ኣድጊያለሁ ይላል። እድገት ብቻ ሳይሆን ልማትም ታይቷል፣ የገበሬው ህይወት ተቀይሯል፣ የሰራተኛው ህይወት ተቀይሯል፣ የማህበራዊ ኣገልግሎት ተሻሽሏል ባይ ነው። ይሁን እንጂ ኣንዳንድ መንግስትን ከፍጹም ተጠያቂነት በተወሰነ ደረጃ ሊያተርፉት የሚሹ ኣካላት እድገት ኣለ ነገር ግን ልማታዊ ያልሆነ እድገት ነው ያለው ይላሉ። ይሁን እንጂ ኣብዛኛው ህዝብ ይህ ክርክር ኣንጀቱ ጠብ ኣይልም። ዋናው ጉዳይም ይሄ ኣይደለም። ይልቅ ፍትሃዊው ጥያቄ መንግስት እድገት ኣለ ከኣፍሪካም ከዓለምም ኣንደኛ ወጥተናል ካለ እሺ በጣም ጎበዝ ደስ ይለናል በል እንግዲህ ያንን እድገት በገበታችን በገቢያችን ላይ ኣሳየን፣ በማህበራዊ ተቋምት ኣቅርቦት ስፋት ኣሳየን የሚለው ጥያቄ ሚዛን ይደፋል። በመጀመሪያ ግን ኣንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንዳሉት መንግስት እድገት ኣለ ሲል እድገቱ ከየት እንደመጣ ይጠየቃል። ከመንግስት ኣካላት ውስጥ የሚሰሙ ካሉ ይመልከቱት:: መንግስት የሚለው ለዚህ እድገት ግዙፉን ድርሻ የተሸከመው ግብርናው ነው። ግብርና መር ፖሊሲ እንዳለው የሚናገረው መንግስት ግብርናችን ኣገራችንን በጥንድ ቁጥር ኣሻግሯል የሚል ነው። እዚህ ላይ ታዲያ ኣጥብቆ ጠያቂዎች ጠይቀውታል። ለመሆኑ ግብርናው ሃገሪቱን ለኣስር ኣመት ዝንፍ ሳይል እንዲህ ለማሳደግ የሚችለው እንዴት ነው? ቢያንስ በግብርናው መሪነት ከፍተኛ ለውጥን ለማሳየት የሚከተሉት ጉዳዮች መገምገም ኣለባቸው።
.
ኣንደኛው ገበሬው ዘምኗል ማለት ነው። የጎልማሶች ትምህርት ተሻሽሎ ገበሬው ቴክኖሎጂዎችን የመቀበል ኣቅሙ ዳብራል ማለት ነው። ከትምህርት የተነሳ ኢኖቬቲቭ ሆኗል ማለት ነው።
ሁለተኛ ብዙ ያልታረሱ ለም መሬቶች ታርሰዋል ማለት ነው። ምርት ይጨምር ዘንድ ኣንዱ ነገር ገበሬው እርሻውን ማስፋት ችሏል ማለት ነው።የመስኖ ልማት ተስፋፍቷል ማለት ነው።
ሶስተኛ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ተሻሽሎ የመሬቱ ለምነት ጨምሯል ማለት ነው
አራተኛ ከፍተኛ የሆነ የእርሻ ግብዓት፣ እንደ ዩሪያ፣ ዳፕ፣ምርጥ ዘር፣ ፔስት ሳይድ፣ የምርት መሳሪያዎችን ተጠቅሟል ማለት ነው።
ኣምስተኛ የግብርና ምርት ውጤት ኤክስፖርት በጣም ኣድጓል ማለት ነው።
እነዚህን ነጥቦች ስንገመግም በርግጥ ግብርናው ይህን ጥንድ ቁጥር እድገት ኣምጥቷል ወይ የሚለውን መላምት እውነትነት ያረጋግጥልናል። በኣጭሩ ለማየት ያህል የጎልማሶች ትምህርትን በተመለከተ በደርጉ ጊዜ ተጀምሮ የነበረው የመሰረተ ትምህርት ፕሮግራም በዚህ መንግስት በመደምሰሱ ማንበብና መጻፍ የጀመሩ ጎልማሶች 60% ደርሶ የነበረው በኣሁኑ ጊዜ መጻፍና ማንበብ ጀምረው የነበሩ ሁሉ ወደ መሃይምነት ተመልሰው ወደ 37.5% ዝቅ ብሏል። ይሄ በዓለም ኣልታየም:: በዚህ በኩል መንግስት ገበሬውን ኣክስሮታል እንጂ ኣላተረፈም ስለዚህ ዘመናዊ ትምህርት በዚህ እድገት ውስጥ ሚናው ኣይታይም። በርግጥ የልማት ሰራተኞችና የግብርና ባለሙያዎች ገበሬውን በሙያ ለማገዝ ይጥራሉ ይሁን እንጂ ባለመማሩ ቴክኖሎጂን በቀላሉ በመቀበሉ ላይና በፈጠራ ኣቅሙ ላይ ጉልህ ሚና ይጫወት የነበረው ትምህርት ኣላደገምና በዚህ በኩል ለዚህ እድገት ትምህርት ኣስተዋጾው የለም ማለት ነው።
ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ምርት ሊያድግ የሚችለው በርግጥ የገበሬው ይዞታ ተስፋፍቶ ያልታረሱ መሬቶች ታርሰው ከሆነ ነው። የሃገሪቱን ዋና ዋና ምርት በተመለከተ ከ90% በላይ የሚሆነውን ምርት የሚያመርተው ገበሬ በኣማካይ ኣንድ ሄክታር መሬት የሚያርሰው ገበሬ ነው። ታዲያ እጅግ ብዙውን የሚያመርተው ያ ኣንድ ሄክታር የሚያርሰው ገበሬ ከሆነና ይህ ገበሬ ደግሞ መሬት መሸጥም ሆነ መግዛት ስለማይችል መሬቱ ኣይሰፋም ኣይጠብምና እንዴት ሆኖ ነው ምርት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምረው። በርግጥ በቆላው ኣካባቢ ሰፋፊ ለም መሬቶች ታርሰዋል። ነገር ግን ከባለፈው ኣስር ዓመት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ለም የሆኑ መሬቶችን መንግስት ለመሬት ነጣቂዎች በመስጠቱ እነዚህ መሬቶች ታረሱ ማለት የሃገሪቱን ምርት ሊያሳድጉ ነው ማለት ኣይቻልም። ስለሆነም ያን ያህል ከባድ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል እርሻ በኣነስተኛ ያዡ ገበሬ ዘንድ ስላልሰፋ ያን ያህል ምርት ተመረተ ለማለት ኣይቻልም።
.
በግብርና ኤክስፖርቶቻችን ዘንድ ብዙ የምንደገፍ ሲሆን ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ውጤቶች ተደማምረው ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ነው የምናገኘው። የሚያሳዝነው መንግስት ራሱ ወደብ ኣልባ ያደረጋት ኢትዮጵያ ይህቺን ለፍታ ጥራ የላከቻትን የግብርና ምርት ገቢ መልሳ ለወደብ ትከፍላለች። እዚያው ወደብ ላይ የውጭ ንግዳችን ይቀራል። ጂቡቲ ከፍተኛውን ድርሻ ስትይዝ፣ ሱዳን፣ ሶማሌላንድና ኬንያም ትንሽ ትንሽ ይካፈሉናል። ገማቾች እንደሚሉት ለጂቡቲ ብቻ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለወደብ እንከፍላለን። ይህ ደግሞ በልማት ላይ ከባድ ተጽእኖ ኣለው።
የማዳበሪያና የእርሻ ግብዓቶችን ጉዳይ ስናይ ደግሞ ፍላጎቱ የጨመረ ቢሆንም ያን ያህል ከባድ ለውጥን ሊያመጣ የሚችል እድገት እንዳላሳየ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በሌላ በኩል በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ሜትሪክቶን ለም ኣፈር እየታጠበ የሚሄድባት ኣገር በመሆኗ እርሻው የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለመለወጥ ጉልበት ያንሰዋል:: ሃገሪቱ የመስኖ ልማትን ችላ ያለች በመሆኗ ዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ በሆነ ግብርና ይሄን ያህል እድገት ማምጣት ኣይቻልም። ኣስር በመቶ የሚሆነውን እንኳን በመስኖ ማልማት ያልቻለ መንግስት ግብርናው ኣደገ ማለት ተቀባይነት የለውም። ኢትዮጵያ ከብዙ ሃገራት የተሻለ የዝናብ መጠን በዓመት በዓማካይ ብታገኝም ስርጭቱ ችግር ስላለበት ማለትም ኣንዳንዴ በሃይል ይወርድና መሬቱን ይሸረሸራል፣ ኣንዳንዴ በቂ ዝናብ ኣይዘንብምና የግድ በከርሰ ምድርና በመስኖ ካልተደገፈ ግብርናው የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ቀርቶ ጎታች ነው የሚሆነው። የእስንሳት ሃብታችንን ስናይ ምንም እንኳን በቁጥር ከኣፍሪካ ኣንደኛ ብንሆንም ነገር ግን የተሻሻለ መኖ ባለመኖሩና ርባታው ባለማደጉ በግብርናው ላይ ይሄ ነው የሚባል ጉልህ ተጽእኖ ኣያመጣም። በኣጠቃላይ የግብርናውን ጓዳ ጎድጓዳ ስናይ ይሄን ያህል ኣመርቂ የሆነ ውጤት ከግብርናው ሊገኝ የሚያስችል ሁኔታ የለም። ከፍ ሲል እንዳልነው ዘጠና ዘባት በመቶ የሆነውን ሰብል የሚያመርተው ገበሬ መሬቱ ኣይሰፋም ኣይጠብም። ኣይሸጥም ኣይገዛምና ይህ በሆነበት ኣገር ምርት የሚፈለገውን ያህል ሊጨምር ኣይችልም።
.
መንግስት ኢንዱስትሪው ነው ይህን ለውጥ ያመጣው ብሎ ስላልተከራከረ ብዙ ማለት ኣያስፈልግም። ኢንዱስትሪውና ማንፋክቸሪንጉ ያለው ኣስተዋጾ ገና ስላላደገ ኣምስት በመቶ የሚሆን ኣስተዋጾ እንኳን ስለሌለው ይህ ጥንድ ቁጥር እድገት ከዚያ ኣካባቢም እንዳልመጣ ይታወቃል። ሰርቪስ ሴክተሩ ከግብርናው ቀጥሎ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የተሸከመ ቢሆንም ይህም በሃጋሪቱ ውስጥ ኣሁን የሚነገረውን ጥንድ ቁጥር ያለው እድገት ለማምጣት ኣይችልም። በመሆኑም ይህ እድገት ከየት መጣ? ተብሎ መንግስት ቢጠየቅ ምላሽ ኣይኖረውም። በጣም ሲበሳጭ እድገት ማሳያ ብሎ የሚገልጸው ኣንዱ የመንገዶች ስራና ከተሞች ኣካባቢ ያሉ የኢንፍራስትራክቸር ለውጦችን ነው። በርግጥ የሚታዩ እነዚህ መንገዶችና ህንጻዎች ከዚህ ከጥንድ ቁጥሩ ጋር በተያያዘ የመጡ እድገቶች ኣይደሉም። ይህ የሚታየው መንገድ ስራ በኣብዛኛው በእርዳታና በብድር የሚሰራ ነው። ኣንጻራዊ በሆነ መንገድ የማህበራዊ ተቋማት ግንባታዎች ቢታዩም በኣብዛኛው ከብድርና እርዳታ ጋር የተገናኙ ናቸው እንጂ የእድገቱ ውጤቶች ኣይደሉም። ገና ኢትዮጵያ የዛሬ ሰላሳ ኣርባ ኣመት የምትከፍለው የብድር እዳ ነው።
መቼም ስለ እድገት ስናወራ ስለ ኢኮኖሚ ልማት ማንሳት የግድ ነውና መንግስት በኢኮኖሚ ልማት በኩልም ተሳክቶልኛል ይበል እንጂ ከእድገቱ ባለ ድርሻ ሊሆን የሚገባው ሰፊ የሆነው ገበሬ ይህ የጥንድ ቁጥር እድገት ኣርሶታል ወይ? ካልን ችግሩ ደግሞ በገበሬው ይብሳል። ከፍ ሲል እንዳልኩት ገበሬው የመሬት ባለቤት ባለመሆኑ ከይዞታው ኣይፈናፈንም። ይዞታው ኣይጨምርም። የገጠመው ችግር ምንድን ነው? ልጆች ይወልድና ሲደርሱ ይሻሙታል። ያቺኑ መሬት ስድስት ቤተሰብ ይዞ ይኖራል። ኑሮው ከእጅ ወደ ኣፍ ብቻ ይሆንበታል። ኣንዳንዴም ከዚያች ቁራጭ መሬት ላይ የሚያገኘው እህል ኣመቱን ሙሉ ስለማይመግበው እርዳታን ጠባቂ ይሆናል። ከሁለት እስከ ኣራት ወር በዓመት ርዳታን ይፈልጋል። በመሆኑም የገበሬው ኑሩ ዛሬ ከመቼውም የበለጠ ከፍቷል። እንደ ድሮው ልጁን ትምህርት ቤት ልኮ ልጁ ኮሌጅ በጥሶ ደመወዝ ቆርጦ ይጦረኛል የሚል ተስፋ የለውም። ኣስተማሪው ልጁ እንኳን ኣባትና እናቱን ሊረዳ ራሱንም ትዳር ያንገዳግደው ይዟል። አብዛኛው ገበሬ በተለይ በደጋ ያለው ኑሮው ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል።አንዱ ለዚህ ችግር የዳረገን ነገር በርግጥ የህዝብ ብዛትም ነው። መንግስት በቤተሰብ እቅድ ረገድ የሰራው ስራ የለም። ይህ መንግስት ስልጣን ከያዘ ወዲህ ባለፉት ሃያ ኣምስት ኣመታት ብቻ የኢትዮጵያ ህዝብ በሃምሳ ኣምስት ሚሊዮን ጨምሯል። የሚገርመው ነገር በዚህ ሃያ ኣምስት ኣመት የመጨመረው ህዝብ ብዛት የኣፍሪካን የኣስራ ኣምስት ኣገራትን ህዝብ ተደምሮ ያክላል። እነዚህ ኣሃገራት ሴራሊዩን፣ሊቢያ፣ማእከላዊ የኣፍሪካ ሪፐብሊክ፣የኮንጎ ሪፐብሊክ፣ሞሪታኒያ፣ናሚቢያ፣ቦትስዋና፣ጋምቢያ፣ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ሌሴቶ፣ጋቦን፣ጊኒ ቢሻው፣ሞሪሺየስ፣ስዋዚላንድ ናቸው። የነዚህ ሃገራት ህዝብ በሙሉ ተደምሮ ወያኔ ከመጣ የጨመረውን የህዝብ ብዛት ያክላል። የነዚህ ኣገሮች የቆዳ ስፋት ተደምሮ የኢትዮጵያን ኣምስት ጊዜ ያክላል። የሰው መብዛት በኣንድ በኩል ሃይል ቢሆንም ነገር ግን በዚህ የመሬት ፖሊሲ በታሰረች ኣገርና በብሄር ፌደራሊዝም በተኮለኮለች ኣገር እንዲሁም ኢኮኖሚው ከህዝብ ብዛቱ ጋር ኣብሮ በማያድግበት ኣገር ህዝቡን ለድሃነት የሚያጋልጥ ነገር ነው።
.
በኣጠቃላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ስናይ መንግስት በጥንድ ቁጥር እያደግን ነው ቢልም ይህ እድገት ግን በዘዴ ሲቪሉን ሰራተኛ ደሙን እየመጠጠ ያለ ነው። ሰፊውን ገበሬ ደሙን እየመጠጠ ያለ ነው። ኣነስተኛ የሆኑ ነጋዴዎች ከህወሃት የንግድ ድርጅቶች ጋር መወዳደር ስለማይችሉ የነሱንም ደም የመጠጠ ነው። መንግስት ይህንን ያፈጠጠ እውነት ምንም ሊያደርገው ኣይችልም። እጅግ ብዙ ድሃዎችን እያፈሩ፣ የሲቪል ሰራተኛውን ጉልበት እየሰረቁና ሃብት በዘዴ እያዛወሩ ኣንድ የጠገበ ሃብታም ማፍራት እድገት ኣይደለም። ስለሆነም ኣሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚታዩ ግንባታዎች ከሙስና የተራረፉ የብድርና የእርዳታ ውጤቶች ሲሆኑ ሌላው የሃገሪቱ ሃብት ግን እንደነ ኤፈርት ኣይነቶቹ የህወሃት ድርጅቶች ሰብስበውት ይታያል። በዚህ መሃል በጣም የተጎዳው ሲቪል ሰራተኛውና ገበሬው እንዲሁም ድሃው ነጋዴ ነውና ይህ የህብረተሰብ ክፍል ለለውጥ መነሳት ይኖርበታል፡፡

download

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: