ገመና ገላጭ የፓናማ ሰነዶች… | ከበፍቃዱ ኃይሉ

ከአዘጋጁ: ይህ ጽሁፍ በዞን 9 አባላት በፈቃዱ ኃይሉና ዘላለም ክብረት አዘጋጅነት ባለፈው ቅዳሜ በኢትዮጵያ ታትማ በወጣችው ‘ውይይት’ መጽሄት ላይ ታትሞ ወጥቷል:: ውጭ ያለው አንባቢ በድረገጽ እንዲያነበው ታስቦ የቀረበ::

ከበፍቃዱ ኃይሉ

በ1999፣ ኢትዮጵያ በድኅረ ምርጫ 97 ቀውስ እየተናጠች በነበረችበት ጊዜ ዓለምዐቀፉ ማኅበረሰብ “ለአፍሪካ ዴሞክራሲ ተስፋ ሰጪ መሪ” ሲሏቸው የነበሩት የቀድሞው የኢ.ፌዲ.ሪ. ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መልካም ሥማቸው እየደበዘዘ ነበር። በዚህ መሐል የያራ ፋውንዴሽን ዓመታዊ ሽልማት የመጀመሪያው ተሸላሚ መሆናቸው ሲታወጅና ዜናውን የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች ሲያራግቡት በወቅቱ ስርጭታቸው ያልተቋረጡት ነጻ ጋዜጦች ደግሞ ሽልማቱን በሽሙጥ ነበር የተመለከቱት። በተለይም ኢትዮጵያ የያራ ኢንተርናሽናል የማዳበሪያ ደምበኛ ከመሆኗ አንጻር “ሽልማቱ ለማዳበሪያ ደምበኝነቱ የተሰጠ ሙስና ነው” እስከ ማለት የደረሱም ነበሩ።

ያራ ፋውንዴሽን ለግብርና አስተዋፅዖ የሚያግዙ ኬሚካሎችን በማምረት የሚታወቀው ያራ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዋና መቀመጫው ኖርዌይ የሆነ ዓለምዐቀፍ ኩባንያ የሚደጎም “አረንጓዴ ልማትን” አበረታታለሁ የሚል ተቋም ነው። የያራ ኢንተርናሽናል የማዳበሪያ ደምበኝነቱም ይሁን የያራ ፋውንዴሽን የሽልማቱ ትሩፋት አሁንም ድረስ (ሽልማቱ ከተጀመረ በ10 ዓመቱ) ወደ ኢትዮጵያ መዝለቁን ቀጥሏል። እ.አ.አ. በ2014 ግብርና ሚኒስትሩ ፕ/ር ተካልኝ ማሞ፣ በ2012 ዶ/ር እሌኒ ገ/መድኅን የሽልማቱ ተቋዳሽ ሆነዋል።

ያራ ኢንተርናሽናል በተለያዩ አገራት የገበያ የበላይነት ለማፍራት የአገር መሪዎችን በሙስና እንደሚደልል መረጃዎች አሉ። በተለይም አራት የሥራ አስፈፃሚ አባላቱ በሕንድ እና በሊቢያ የገበያ ጣምራ ስምምነት ለመመሥረት ለባለሥልጣናት እስከ 8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድረስ ጉቦ በመስጠታቸው በኦስሎ፣ ኖርዌይ ፍርድ ቤት ቀርበው ሐምሌ 2007 “ጥፋተኛ” ሆነው በመገኘታቸው ወደወኅኒ መላካቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከዚያም በፊት በ2003 በተመሳሳይ የሙስና ወንጀል የ35 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተጥሎበት ነበር።

የየራ ሽልማት በተለይ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሽልማቱን ባበረከተበት ወቅት “እንደኮሚሽን” ቢታይም ይህ ነው የተባለ ማስረጃ አልተዘረዘረበትም። ይሁን እንጂ ሰሞኑን ያራ ኢንተርናሽናል በታላቁ የቢዝነስ ቅሌት ውስጥ ባለፈው ወር ይፋ የሆኑትን የፓናማ ሰነዶች ጋር በተያያዘ ሥሙ ተነስቷል። ይህ የቢዝነስ ቅሌት የእኛንም አገር አንኳኩቶ ይሆን እንዴ የሚለውን ለአንባቢ በመተው የሰሞኑን ቅሌት ነጥለን እንመለከታለን።

የፓናማ ሰነዶች…

የፓናማ ሰነዶች የሚባሉት መጋቢት 28፣ 2008 ‹ሞሳክ ፎንሴካ› ከተባለው የኮርፖሬት ጥብቅና ድርጅት ተሰርቀው ይፋ የተደረጉ 11.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ምስጥራዊ የታክስ ማጭበርበር ሰነዶች ናቸው። ሰነዶቹ በታክስ ማጭበርበር ቅሌቱ የተነካኩ 214 ሺሕ ኩባንያዎችን ሚስጥር አደባባይ ላይ በትነዋል ተብሎላቸዋል። በሰነዶቹ ከአርባ በላይ አገሮች እና የተለያዩ የአገር መሪዎች፣ ዓለምዐቀፍ ኮርፖሬቶች፣ ባለሀብቶች እና ሌሎችም መነካካታቸው ተጋልጧል። ሰነዶቹን ያጋለጣቸው ራሱን ጆን ዶ በተባለ የሽፋን ሥም የሚጠራ ግለሰብ ‹ሱዴሽ ዜተንግ› ለተባለ የጀርመን ጋዜጣ በተከታታይ በላካቸው ሰነዶች ነው። ከሰነዶቹ ብዛት የተነሳ ጋዜጣው ሰነዶቹን ይፋ ከማድረጉ በፊት የዓለምዐቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ኅብረትን (International Consortium of Investigative Journalists (ICIJ) 400 ያህል ጋዜጠኞችን በማሳተፍ አስፈላጊዎቹን መረጃዎች በርብረውና አጥልለው እንዲያወጡ የተወሰነ ጊዜ ወስዷል።

እነዚህ እስከዛሬ ተሰርቀው ከተጋለጡ ሰነዶች ሁሉ በብዛታቸው ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው ‹የፓናማ ሰነዶች› ገመናቸውን አደባባይ ካወጡባቸው ዓለምዐቀፍ ኩባንያዎች መካከል ይኸው የኢትዮጵያ መንግሥት የማዳበሪያ ደንበኛ ያራ ኢንተርናሽናል አንዱ ነው።

ያራ ኢንተርናሽናል በፓናማ ሰነዶች ውስጥ…

አፍተንፖስተን የተባለ ጋዜጣ ይፋ እንዳደረገው፣ ያራ በሕግ ያልተጠየቀባቸው ተጨማሪ ሙስናዎች ውስጥ ተዘፍቆ እንደነበር የፓናማ ሰነዶች አጋልጠዋል። እንደሪፖርቱ፣ ያራ ለራሺያው ዩሮኬም የተባለ ደርጅት ማኔጀሮች 2.6 የአሜሪካ ዶላር እ.ኤ.አ. በ2004 እና 2009 ሰጥተዋል። ይህንን ጉቦ እንደተቀበሉ አሁን በሰነዱ የተጋለጡት ማኔጀሮች በድርጅቱ ተጠርጥረው ከተባረሩ በኋላ ኩባንያውን የሚያከስር ስምምነት አድርጋችኋል የሚል የ40 ሚሊዮን ዶላር ክስ የተመሰረተባቸው ቢሆንም፣ በወቅቱ ማስረጃ ሊገኝባቸው ባለመቻሉ በነጻ ተሰናብተው ነበር።
የፓናማ ሰነዶች ግን ያንን የተድበሰበሰ ምስጢር አጋልጠዋል። የያራ ኃላፊዎች ስለዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ፣ ‹ተገቢ ያልሆኑ ክፍያዎችን› ፈፅመው የነበረ መሆኑን አምነው ‹ያለፈ እና የተቀጣንበት ነው፤› በማለት ማብራሪያ ሳይሰጡበት እንደቀሩ አፍተንፖስት ዘግቧል። ይሁን እንጂ ያራ በዚህንኛው ወንጀሉ ያልተጠየቀበት መሆኑን ጋዜጣው ጨምሮ ጠቅሷል። የኖርዌይ ፖሊስ በበበኩሉ ገንዘቡ የተላከው ከስዊዘርላንድ ወደራሺያ በመሆኑ ኖርዌይ በጉዳዩ ላይ የሕግ እርምጃ መውሰድ የምትችልበት መንገድ አላገኘችም ብሏል። ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ በእንደዚህ ዓይነት ሙስና የተርመጠመጠው ያራ ኢንተርናሽናል የኖርዌይ መንግሥት ከ36 በመቶ በላይ በባለድርሻነት የያዘው መሆኑ ነው።

የፓናማ ሰነዶች እነማንን ገፋ …

ያራ ለራሺያው ኩባንያ የፈፀመውን ተገቢ ያልሆነ ክፍያ አስፈፅመዋል የተባሉት ማይክል ግራመር፣ የሀይፖ ላንድስባንክ ፎራልበርግ ሊቀመንበር፣ ሥልጣናቸውን “በሚዲያ ግፊት” ለቀዋል። ነገር ግን በፓናማ ሰነዶች ሰበብ ሥልጣናቸውን ያጡት ሚስተር ግራመር ብቻ አይደሉም። የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ገንላውግሰን ቤተሰባቸው የታክስ አጭበርባሪ ድርጅት ባለቤት መሆኑ ስለተጋለጠ ሥልጣናቸውን አጥተዋል። የስፔን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ጆዜ ማኑኤል ሶሪያ የሼል ኩባንያ ከታክስ ማጭበርበሩ ጋር በተያያዘ በፓናማ ሰነዶች በመጋለጡ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገድደዋል። ሌሎችም በተመሳሳይ መንገድ ሥራቸውን አጥተዋል፤ ለሕግ ተጠያቂነት የሚቀርቡ አሉ። በፓናማ ሰነዶች ውስጥ ሥማቸው የተጠቀሱ አሜሪካውያን አራት ብቻ ሲሆኑ እነርሱም ቀድሞውኑ በሕግ የተጠየቁ ናቸው።

ከፓናማ ሰነዶች ጋር በተያያዘ ሥማቸው ከተጠቀሱ ታላላቅ መሪዎች ውስጥ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ይገኙበታል። ካሜሩን ይልቀቁ የሚል ከፍተኛ ጫና ከተቃዋሚዎቻቸው ቢሰነዘርም እስካሁን የሚያስለቅቃቸው ደረጃ አልደረሰም። ነገር ግን የፓናማ ሰነዶች መዘዝ ወንበሮችን ነቅንቆ የሚያልፍ ብቻ እንደማይሆን ብዙዎች ግምታቸውን ከወዲሁ እየሰነዘሩ ነው።

ፎሪይን ፖሊሲ የተባለው የድረገጽ ጋዜጣ የሰነዶቹን ተፅዕኖ የሚያወዳድረው ‹የሼል ባንኮችን ካከሰመው 9/11 የሽብር ጥቃት ወይም የኢኮኖሚ ትብብርን ካስገደደው እ.አ.አ. የ2008 ዓለማዐቀፍ የፋይናንስ ቀውስ› ጋር ነው። ትልልቅ ኩባንያዎች ታክስ እያጭበረበሩ ወይም እየሸወዱ መቀጠል የማይችሉበት ሁኔታ ወደፊት እንደሚፈጠር የብዙዎች ግምት ነው። የፓናማ ሰነዶች ይፋ ከመሆናቸው በፊት፣ በዚሁ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መባቻ ላይ የእንግሊዙ ኦክስፋም የትልልቅ ኮርፖሬቶች ታክስ ማጭበርበር በዓለምዐቀፍ ደረጃ መቅረፍ ላልተቻለው የሀብት ክፍተት (wealth gap) ዋነኛ ሰበብ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል።

ምንጭ: ውይይት መጽሔት

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: