ከ30 በላይ ህገወጥ ተቋራጮች የ40/60 መርሃግብር ቤቶችን እየገነቡ ነው

መረጃ እንደሚያሳየው፥ በቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ሳይመዘገቡ እና ማጣሪያ ሳይወስዱ ሰባት ተቋራጮች አሁን ግንባታ ላይ ናቸው።

— በኢንተርፕራይዙ ተመዝግበው ማጣሪያው ላይ ያልተሳተፉ 12 ተቋራጮች በመርሃ ግብሩ ቤቶች እየገነቡ ነው።

— የቴክኒክ ብቃታቸው ዜሮ ነው የተባሉ አምስት ተቋራጮች ደግሞ እዚሁ ስራ ላይ አሉ።

— ሙሉ በሙሉ ስልጠና ያልወሰዱ ሁለት፣ የሀሰት ፍቃድ ያላቸው ስምንት ተቋራጮች በጥቅሉ 34 ተቋራጮች በህገ ወጥ መንገድ ገብተው የ40/60 ቤቶችን በመገንባት ላይ ናቸው።

በመርሃ ግብሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ህገወጥ ተቋራጮች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያድግ እንደሚችል ነው የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ አቶ ሀይሉ ቀንአ የገለጹት።

ተቋራጮች ወደ ስራ እንዴት ነው የሚገቡት?

አዲስ አበባ በ40/60 መርሃ ግብር ከ38 ሺህ በላይ ቤቶች እየተገነቡባት ነው።

እነዚህን ቤቶች የሚገነቡ ከ100 በላይ ተቋራጮች ደግሞ አሁን በስራ ላይ ናቸው።

ይህንን ሰራ የሚያከናውኑ ተቋራጮች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት በቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በማምራት ይመዘገባሉ፤ ከዚያም ስልጠና ይወስዱና ይገመገማሉ።

ግምገማው አቅማቸውንና ህጋዊነታቸውን የሚመለከት ሲሆን ፥ ማጣሪያውን ያለፉ ተቋራጮች ወደ ስራ ይገባሉ።

ህጋዊው አሰራር ይህ ሆኖ ሳለ በመስሪያ ቤቱ ባልደረቦችና በደላሎች አማካኝነት ድርድር ይቀርብልናል ይላሉ አስተያየታቸውን የሰጡን ተቋራጮች።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ፥ በቤት ልማት ፕሮግራሙ ላይ የተቋራጮች የስራ ስምሪት በጨረታ ሳይሆን ቁርጥ ዋጋ ተቀምጦላቸው በደረጃቸው መሰረት ነው የሚከናወነው ብለዋል።

በ40/60 መርሃ ግብርም ከደረጃ 1 እስከ 3 ያሉ የስራ ተቋራጮች ናቸው እንዲሳተፉ የሚፈቀድላቸው ያሉት ሀላፊው፥ ግልፅ የሆነ መመሪያ እና መስፈርት የሌለ መሆኑ ይህን መሰሉን ችግሩ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ወደ ስራ የሚገቡ ተቋራጮችን መቆጣጠር በዋናነት የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ሀላፊነት ነው ባይ ናቸው አቶ ይድነቃቸው።

ከ30 በላይ ህገወጥ ተቋራጮች እየተሳተፉበት ያለው የ40/60 መርሃ ግብር ከተጀመረ ሁለት አመት አልፎታል።

ኢንተርፕራይዙም እነዚህን ህገወጦች እየለየ መሆኑንና ለህግ ለማቅረብ ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የኢንተርፕራይዙ ስራ አስኪያጅ አቶ ሀይሉ ቀንአ፥ “ወደዚህ ሀላፊነት ከመጣሁ አጭር ጊዜ ነው፤ ከአሁን በፊት በነበረው አስተዳደር የተፈጠሩ ችግሮችን በማስተካከል ላይ ነኝ፤ ከሁለት አመት በላይ ለዘለቀው ችግርም መፍትሄ እያፈላለግን ነው” ብለዋል።

ለህገወጥ ተቋራጮቹ መብዛት የፈቃድ አሰጣጡ ጉድለት አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ያነሳንላቸው የከተማዋ ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ዮናስ አያሌውም፥ “ቢሮው ከተቋቋመ አራት ወሩ ነው፤ ችግሩ ደግሞ ከሁለት አመት በላይ ሆኖታል” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

በተቋራጮቹ የሚገነቡ ቤቶች ጥራት ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

እነዚህ ህገወጥ ተቋራጮች በሚገነቧቸው ቤቶች ጥራትም ሆነ ፍጥነት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ የሚጠበቅ ነው።

የከተማዋ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ ግን ከጥራት ጋር በተያያዘ የከፋ ጉዳት አያደርሱም ባይ ናቸው።

ለዚህም ለግንባታ የሚውሉ ግብአቶች ሙሉ በሙሉ በመንግስት የሚቀርቡ መሆናቸውን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ።

ተቋራጩ የጉልበት እና ሙያ ስራ ብቻ ነው የሚያከናውነው፤ የክትትል እና ፍተሻ ስራ ስለሚከናወንም የጥራት ችግር አይፈጠርም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ህገወጥ ተቋራጮቹ ተለይተው ለህግ ሊቀርቡ እንደሆነም የስራ ሀላፊዎቹ ነግረውናል።

ተቋራጮቹን በዚህ መልኩ በፕሮጀክቶቹ ላይ እንዲሳተፉ አድርጋችኋል የተባሉ የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ሰራተኞች እና አመራሮችም በተመሳሳይ ከሀላፊነት እንዲነሱ፣ እንዲታገዱ እና በህግ እንዲጠየቁ መደረጉንም ነው የገለጹት።

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: