ፓትርያሪክ አቡነ ማቲያስ “እስከምሞት እዋጋዋለኹ፤ እጅ እግሩን አስረዋለኹ” ሲሉ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ዛቱ –

Dn . Abayneh kassie
በአወዛጋቢ ውሣኔዎቹ እየታወቀ የመጣው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ከመሻሻል ይልቅ ቁልቁል መውረዱን ሥራየ ብሎ የተያያዘው እንደኾነ ሂደቶቹ ኹሉ ምስክሮች ናቸው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነው በኅዳር ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. በቁጥር 951/16187/2008 ማኅበረ ቅዱሳን “ኢቢኤስ” እየተባለ በሚጠራው የሳተላይት ቴሌቪዥን ያሠራጭ የነበረውን መርሐ ግብር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ነው፡፡

ፓትርያርኩ ራሳቸው ፈርመውበት ባወጡት ደብዳቤ ለጥያቄው ምላሽ ሲሰጡ የተጠቀሙት ቃል እጅግ አነጋጋሪ እና በቸልታ ሊታይ የማይገባ ነው፡፡ በቀን ፳፫/፫/፳፻፰ በቁጥር ል/ጽ/117/ 300/2008 ግልባጭ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በማድረግ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ እውን ቀኖናዊት፣ ሐዋርያዊት ከኾነች ቤተ ክርስቲያን ጽ/ቤት የሚወጣ ነውን? ያሰኛል፡፡

ደብዳቤው “የማኅበሩ ሕገ ደንብ ቀርቦ ያልጸደቀ ከመኾኑም በላይ” የሚል ማጣፊያ ያጠረው ሐረግ በዋና ማብራሪያነት ተሰንቅሮ ይነበብበታል፡፡ ይህ አባባል በጥቂቱ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ይታዩበታል፡፡ አንደኛው የማኅበሩን ሕልውና መካድ እና ሁለተኛው ኢ-ቀኖናዊነት!

በእርግጥ ማኅበሩ ደንቡ እንዲሻሻልለት ለሚመለከተው አካል አቅርቦ በተሰጠው ይሁንታ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶበት ውክልና በተሰጠው አካል እየታየ መኾኑ ይታወቃል፡፡ ይኽ ማለት ግን ማኅበሩ አሁን “ደንብ አልባ” ነው ማለትን ፈጽሞ አያስከትልም፡፡ አሠራርን የማያውቁ አካለት እንዲህ ብለው ቢናገሩ አለማወቅ ነው ይባል ነበር፡፡ “ሕግ ይወጽእ እም ጽዮን” የሚባልላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለዚህ አሠራር እንግዳ አይደለችም፡፡ ደረጃዋን ያገናዘበ ተዋናይ ካላጣች በስተቀር!

በረቂቅነት ቀርቦ በመታየት ላይ ያለው ደንብ እስኪሻሻል ድረስ ነባሩ ሕገ ደንብ እንደሚሠራ በየትኛውም አሠራር የታወቀ ነው፡፡ ነባሩ ሕገ ደንብ እንዳይሠራ የሚወሠንበት ጊዜም አለ፡፡ እርሱም በቂ ምክንያት ቀርቦበት ሥልጣን ባለው አካል ጊዜአዊ ማዕቀብ /Temporary Suspension/ ሲደረግበት ነባሩ ሕግ ለተወሰነ ወይም ላልተወሠነ ጊዜ እንዳይሠራ የሚደረግባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ ይኸም የሚደረገው ነባሩ ሕግ በሥራ እንዲውል ከተደረገ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ ግምት ውስጥ ያስገባ እንደኾነ ነው፡፡

ሲጀመር ማሻሻያውን የጠየቀው ራሱ ማኅበሩ እንጂ ከላይ በትዕዛዝ መልክ ያልወረደ መኾኑ ምንም ለስጋት የሚያበቃ ክስተት ሊፈጠር እንደማይችል ያመላክታል፡፡ ሲቀጥልም ረቂቁን የተመለከተው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ለዝርዝር ጥናት እና ምልከታ ወደኮሚቴ ሲመራው የታየው ምንም ዓይነት ስጋት ስላልነበር ነባሩን ሕግ ማቀብ አላስፈለገውም፡፡ በዚህ ሁኔታ “የማኅበሩ ሕገ ደንብ ቀርቦ ያልጸደቀ” ነው ብሎ መናገር ከየትኛው ምንጭ ሊቀዳ እንደሚችል ለመገመት ያስቸግራል፡፡ አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው – ከጤናማ አመለካከት እንዳልተቀዳ!

ረቂቁ ሕገ ደንብ ሊሻሻልም ላይሻሻልም ይችላል፡፡ እስከዚ ድረስ ግን ነባሩ ምንም ሳይጨመርበት ምንምም ሳይቀነስበት የመሥራት ሙሉ ሥልጣን አለው፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን የጸደቀ ደንብ ያለው አካል እንጂ በደብዳቤው ላይ እንደተባለው ደንብ አልብ ማኅበር አይደለም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን መጥላት ሕልውናውን መካድ ሊኾን አይችልም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን መቃወም ማለት ደንብ የለውም ብሎ ከኾነ ራስን ከግምት በታች ማውረድ ይኾናል፡፡ ሰይጣንን መጥላት ማለት ሰይጣን የለም ከማለት ጋር እኩል አይኾንም፡፡ ሰይጣን መኖሩን ዐውቆ ሰይጣንን መቃወም ይገባል፡፡ ሰይጣንን የምንቃወመው በአድማ ሳይኾን በዓላማ ነው፡፡ ስለዚህ ለመቃወማችን በቂ አመክንዮ ለማቅረብ አንቸገርም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን የሚጠሉ ሰዎችም ማኅበሩ የለም ወይም ሕገ ደንብ የለውም ከማለት የሚጠሉበትን ምክንያት ቢነግሩ ምላሹን ባገኙ ነበር፡፡ በሚበቃ ምክንያት የሚጠሉት ወይም የሚቃወሙት ካሉ ከእነርሱ አመክንዮ በመነሣት ራሱን ለማረም ችግር የለበትም፡፡ በማይበቃ ምክንያት የሚጠሉት ካሉ ደግሞ ራሳቸውን እንዲያርሙ ዕድሉን ይሰጣቸዋል፡፡ ከሁለቱ አፈንግጦ “ሕልውናውን መካድ” ግን የማያዋጣ የፈሪ ብትር ይኾናል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ሲጸድቅ በግርግር ሳይኾን ሥርዓቱን እና ደረጃውን ጠብቆ ነው፡፡ መጀመሪያ ረቂቁ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ቀረበ፡፡ መምሪያው ማሻሻያ እና ማረሚያውን ካደረገበት በኋላ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ቀረበ፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስፈላጊውን እርምት እና ማሻሻያ ካደረገበት በኋላ ለቅዱስ ሲኖዶስ ተመራ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው አንቀጽ በአንቀጽ ከተወያየበት በኋላ ተገቢውን ማሻሻያ አድርጎበት በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. አጸደቀው፡፡ በጉባኤው ላይ የነበሩ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፊርማቸውን አኑረውበት ሥራ ላይ እንዲውል ለሚመለከታቸው ሁሉ ተሠራጨ፡፡ ለዚህም ራሴ የዐይን እማኝ ቋሚ ምስክርም ነኝ፡፡

በዚህ ሥርዓታዊ አካሄድ የጸደቀ ሕገ ደንብ ያለውን ማኅበር ደንብ የለውም ብሎ መናገር እንደምን ይቻላል? ደንብ የለውም ብሎ መናገር የማይቻል ከኾነ ደግሞ የለውም ማለት ኢ-ቀኖናዊነት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ራሱ ያጸደቀውን በፊርማው ያተመውን ሕገ ደንብ የለም ብሎ የሚያስብ አካል መኖሩ በራሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ በምልዐተ ጉባኤ የተወሠነን ሕገ ደንብ እንደ ቀልድ በአንዲት ብጣሽ ወረቀት የለም ማለት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሣኔ አልቀበልም ከማለት በቀር ሌላ ፍቺ አንፈልግለትም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለወሠነው ውሣኔ መገዛት እንጂ ማመጽ አይቻልም፡፡ አመጻው ካለ ግን ኢ-ቀኖናዊነት ስለኾነ ፈጣን እርማት ያስፈልገዋል፡፡

ሕልውናው የተካደው ማኅበርም አለሁ ማለት ሳይበጀው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም እርምጃዎቹ ሁሉ ሲደመሩ ወደ አንድ አቅጣጫ እያመሩ እንደኾነ ያሳብቃሉና፡፡ ራሱ ሳይናገር ሌሎች ሊናገሩለት አይችሉም፡፡ እናም መጠበቅ የለበትም፡፡ ምክንያቱም የታሰበበት እና ኾን ተብሎ እየተደረገ ያለ ጉዳይ ስለኾነ፡፡ በማኅበሩ ላይ በዚህ መንገድ የሕልውና ጥያቄ ማንሣት ከመሳሳት በላይ ነው፡፡ “ሕልሙ እና ፍቺው” ከዚህ በጣም ይርቃል፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ ማኅበሩን ለመውጋት ከሚቆሙ አማሳኞች እና ሐራጥቃ ተሐድሶዎች ጋር ለመቆም የማይዳዳው አካል ርቆ ሳይሄድ ሳይቃጠል በቅጠል ሊባል ይገባል፡፡

Advertisements

About Aseged Tamene
Your rights are your security. When you, 'give up your rights for security", it's not security you get, but slavery.'

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: